የጋዜጠኝነትና ስነ ተግባቦት ትምህርት ቤት የጥናትና ምርምር ስራዎች ላይ በትኩረት ሊሰራ ይገባል- የመገናኛ ብዙሃን ባለስልጣን

34

መስከረም 5 /2015 (ኢዜአ) የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የጋዜጠኝነትና ስነ ተግባቦት ትምህርት ቤት ለፖሊሲ ግብአት የሚሆኑ ጥናትና ምርምር ስራዎች ላይ በትኩረት ሊሰራ እንደሚገባ የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር መሀመድ እድሪስ ገለጹ።

የጋዜጠኝነትና ስነ ተግባቦት ትምህርት ቤቱ 25ኛ ዓመት በዓሉን አስመልክቶ የማጠቃለያ መርሃ ግብር አካሂዷል።     

 የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር መሀመድ እድሪስ በመርሃ ግብሩ  ላይ እንዳሉት ትምህርት ቤቱ በተለይም ለፖሊሲ ግብአት የሚሆኑ የጥናትና ምርምር ስራዎች ላይ ትኩረት በማድረግ ሊሰራ ይገባል ብለዋል።         

የአዲስ  አበባ  ዩኒቨርሲቲ የጋዜጠኝነት ትምህርት ቤት በሚዲያው ዘርፍ በርካታ አንጋፋ ባለሙያዎችን ያፈራ መሆኑን ጠቅሰው የሚዲያዎች አቅም እንዲገነባ ስልጠናን ጨምሮ የሚያከናውናቸው የተለያዩ ተግባራትን አመስግነዋል።     

ከዚህ ባለፈ ለአገርና ህዝብ የሚጠቅሙ የጥናትና ምርምር ስራዎች ላይ የበለጠ ሊሰራ ይገባል ብለዋል።  

በተለይም ሚዲያው እንዴት ይሻሻል፣ ምን ሊሰራ ይገባል በሚለው ጉዳይ ላይ በማተኮር መስራት እንዳለበት አመላክተዋል።  

የጥላቻ ንግግርና ሀሰተኛ መረጃዎች ፈተና በሆነበት በአሁኑ ወቅት እውነታንና ትክክለኛ መረጃን ማድረስ በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ማገዝ አለበት ነው ያሉት።  

የትምህርት ቤቱ የሂማኒትስ ቋንቋዎች ጥናት እና ስነ ተግባቦት ኮሌጅ ዲን ዶክተር አማኑኤል አለማየሁ በበኩላቸው ትምህርት ቤቱ ባለሙያዎችን ከማፍራት ባለፈ በምርምርና ማህበረሰብ አገልግሎት ላይ የላቀ ሚናውን እየተወጣ መሆኑን ተናግረዋል።  

በቋንቋ፣ በስነ ጽሁፍና ሌሎች ዘርፎች ትልቅ አሻራ ማሳረፍ የቻሉ ባለሙያዎችን ማፍራቱንም ጠቅሰዋል።

እንደ ዶክተር አማኑኤል ገለጻ ትምህርት ቤቱ በመንግስት መዋቅር ውስጥ ያሉ ባለሙያዎች አቅም መገንባት ላይ ውጤታማ ተግባራት አከናውኗል።

የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የጋዜጠኝነትና የስነ ተግባቦት ትምህርት ቤት ኃላፊ ዶክተር አብዱላዚዝ ዲኖ በበኩላቸው ትምህርት ቤቱ መገናኛ ብዙሃን ላይ የሚስተዋሉ ክፍተቶችን በመለየት ለመፍትሄ ግብዓት የሚሆኑ የጥናትና ምርምር ስራዎች ላይ ትኩረት ማድረጉን ገልጸዋል።  

በተለይም የሦስተኛ ዲግሪ ተማሪዎች ለጥናት የሚያቀርቡት ሀሳብ የሚዲያ ኢንዱስትሪውን በመቀየር በኩል ምን አገራዊ ፋይዳ አለው? የሚለው የሚታይ መሆኑን ተናግረዋል።

የጋዜጠኝነት ታሪክ በኢትዮጵያ ፣እንዲሁም የትምህርት ቤቱ ታሪክና አሁናዊ ሁኔታው በመድረኩ ላይ ሰፊ ውይይት ተደርጎበታል።

የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የጋዜጠኝነትና ሥነ-ተግባቦት ትምህርት ቤት ከ1989 ዓ.ም ጀምሮ ማስተማር መጀመሩ ይታወቃል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም