ከአዲስ አበባ ጋምቤላ አስፓልት መንገድ በመሬት ናዳ በመዘጋቱ መጉላላት ደርሶብናል- አሽከርካሪዎች - ኢዜአ አማርኛ
ከአዲስ አበባ ጋምቤላ አስፓልት መንገድ በመሬት ናዳ በመዘጋቱ መጉላላት ደርሶብናል- አሽከርካሪዎች
ጋምቤላ መስከረም 5/2015 (ኢዜአ) ከአዲስ አበባ ጋምቤላ አስፓልት መንገድ ኩሌሊቴ ተራራ አካባቢ በተከሰተ የመሬት ናዳ በመዘጋቱ መጉላላት ደርሶብናል ሲሉ አሽከርካሪዎች ገለጹ።
በመሬት ናዳ የተዘጋውን የመንግድ ክፍል ለመክፈት ጥረት እየተደረገ መሆኑን በኢትዮጰያ መንገዶች አስተዳደር የጅማ ዲስትሪክት አስታውቋል።
የከባድ መኪና አሽከርካሪ አቶ ታደሰ አስራት ዛሬ ለኢዜአ እንደገለጹት ከጳጉሜ 4 ቀን 2014 ጀምሮ መንገዱ በመዘጋቱ ምክንያት በአካባቢው ተሽከርካሪያቸውን አቁመው እየተጉላሉ ነው።
መንገዱ በመዘጋቱ ምክንያት ከሶስት ቀን በላይ ተሽከርካሪያቸውን አቁመው እየተጉላሉ መሆናቸውን የገለጹት ደግሞ ሌለው የከባድ መኪና አሽከርካሪ አቶ አቡበክር ዳውድ ናቸው።
የሚመለከተው አካል መንገዱን በአፋጣኝ በመክፈት የተስተጓጎለው የተሽከርካሪ እንቅስቃሴ እንዲጀምርና የሚያልፉበትን ሁኔታ እንዲያመቻችላቸው አሽከርካሪዎቹ ጠይቀዋል።
በኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር የጅማ ዲስትሪክት የራስ ኃይል የመንገድ ጥገና ስራ አስኪያጅ ኢንጅነር መሰረት ደጀኔ ስለጉዳዩ ተጠይቀው በሰጡት ምላሽ መንገዱ የተዘጋው በአካባቢው ከጣለው ከባድ ዝናብ ጋር ተያይዞ በተፈጠረ የመሬት ናዳ ነው ።
የተዘጋውን መንገድ ከበዓሉ ዋዜማ ጀምሮ ለመክፈት ጥረት እየተደረገ ቢሆንም በአካባቢው በቂ ማሽነሪ ባለመኖሩ እስካሁን መዘግየቱን ጠቁመው አሁን ላይ ተጨማሪ ማሽነሪዎችን በማስገባት መንገዱን ለመክፈት ጥረት እተደረገ መሆኑን ተናግረዋል።
በቀጣይ በጋ ወራትም መሬቱ ሲረጋጋ መንገዱ በዘላቂነት የሚጠገንበት ሁኔታ እንደሚመቻች ኢንጅነር መሰረት አስታውቀዋል።