ዘላቂ ሰላም ለመገንባት የሃይማኖት አባቶች እና የሀገር ሽማግሌዎች ሚና የጎላ ነው - ሰላም ሚኒስቴር - ኢዜአ አማርኛ
ዘላቂ ሰላም ለመገንባት የሃይማኖት አባቶች እና የሀገር ሽማግሌዎች ሚና የጎላ ነው - ሰላም ሚኒስቴር
ድሬደዋ መስከረም 05/2015 (ኢዜአ) ዘላቂ ሰላም ለመገንባት የሃይማኖት አባቶች እና የሀገር ሽማግሌዎች ሚና የጎላ እንደሆነ የሰላም ሚኒስቴር ገለጸ።
ሚኒስቴሩ ከኢትዮጵያ ሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ጋር በመሆን "ሃይማኖት ለሰላም" በሚል መሪ ሐሳብ በድሬዳዋ እየመከረ ነው።
በምክክር መድረኩ የሰላም ሚኒስቴር አመራሮች፣ የሃይማኖት አባቶች፣ የሀገር ሽማግሌዎች አባ ገዳዎች፣ ኡጋዞች እና የተለያዩ የማህበረሰብ ክፍሎች ተገኝተዋል።
መድረኩን በመልእክት የከፈቱት በሰላም ሚኒስቴር የሀገር ግንባታ መሪ አስፈፃሚ ወይዘሮ አስማ ረዲ፤ ዘላቂ ሰላምን ለመገንባት በሚደረገው ርብርብ የሃይማኖት አባቶች እና የሀገር ሽማግሌዎች ሚና የጎላ ነው ብለዋል።
በመሆኑም ለዚህም ታስቦ ይህ የሰላም ምክክር መድረክ ተዘጋጅቷል ብለዋል፡፡
ሰላምን ለመገንባት ለሚሰሩ ስራዎች የሃይማኖት አባቶችና የሀገር ሽማግሌዎች ከመንግስት ጋር በመሆንና ሰላምን ለማስፈን የሚያደርጉትን ጥረት በማጠናከር የተጀመረው ሀገራዊ የሰላም ግንባታ እንዲቀጥል የበኩላቸውን እንዲወጡ ጥሪ አቅርበዋል።
የኢትዮጵያ ሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ምክትል ጠቅላይ ፀሐፊ ሃጅ መንሱድ አደም በበኩላቸው የሃይማኖት አባቶች የሰላም ባለቤት በመሆናቸው ዘላቂ ሰላም ለመገንባት በሚደረገው ሂደት የበኩላቸውን መወጣት አለባቸው ብለዋል።
የምክክር መድረኩ ዘላቂ ሰላም ለማስፈን እየገጠሙን ያሉ ችግሮችን በመለየት የመፍትሔ ሀሳቦችን በጋራ የምናስቀምጥበት መሆን አለበት ሲሉም ተናግረዋል።
በምክክር መድረኩ "ሃይማኖት ለሰላም ግንባታ" እና "የሃይማኖት እና የመንግስት ግንኙነት" የሚዳስሱ ጽሁፎች ቀርበው ይመከርበታል።