የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎትና የአዳማ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ የሚዲያ አገልግሎትና ሽፋን ጨምሮ በተለያዩ መስኮች በጋራ ለመስራት የሚያስችላቸውን የመግባቢያ ስምምነት ተፈራረሙ - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎትና የአዳማ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ የሚዲያ አገልግሎትና ሽፋን ጨምሮ በተለያዩ መስኮች በጋራ ለመስራት የሚያስችላቸውን የመግባቢያ ስምምነት ተፈራረሙ
መስከረም 5 ቀን 2015 (ኢዜአ)የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት (ኢዜአ) እና የአዳማ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ የሚዲያ አገልግሎትና ሽፋንን ጨምሮ በተለያዩ መስኮች በጋራ ለመስራት የሚያስችላቸውን የመግባቢያ ስምምነት ዛሬ ተፈራርመዋል።
ስምምነቱን የተፈራረሙት የኢዜአ ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ሰይፈ ደርቤና የዩኒቨርስቲው ፕሬዝዳንት ዶክተር ለሚ ጉታ ናቸው።
ስምምነቱ ሁለቱ ተቋማት በአቅም ግንባታ፣በጋራ ፕሮጀክት ቀረጻና ትግበራ፣በሚዲያ አገልግሎትና ሽፋን፣ጉባኤዎችን ማዘጋጀትና የምርምር ስራዎችን በጋራ መስራት የሚያስላቸው እንደሆነ ተገልጿል።
ከተመሰረተ 80ኛ ዓመቱን የያዘው ኢዜአ “በኢትዮጵያ የመጀመሪያ የሆነ” ዘመናዊ የሚዲያ ኮምፕሌክስ አስገንብቶ ሶስት የቴሌቪዥንና አራት የሬዲዮ ስቲዲዮ ስራ ለማስጀመር እየሰራ መሆኑን አቶ ሰይፈ ገልጸዋል።
የመግባቢያ ስምምነቱን ወደ ስራ ለማስገባት የድርጊት ማስፈጸሚያ እቅድ መፈረሙን አመልክተዋል።
ዩኒቨርሲቲው ኢትዮጵያን በሳይንስና ቴክኖሎጂ ወደ ፊት ለማራመድ የሚችል የሰው ኃይል ለማፍራት መሆኑንና ኢዜአ ይሄን ስራ በሙያው ማገዝና መደገፍ አለበት ብለዋል።
ተቋማቱ በተለይም ልዩ ተሰጥኦ ያላቸውን ተማሪዎች ጭምር በውድድር ተቀብሎ በሳይንስ፣ቴክኖሎጂና ኢንጅነሪንግ ዘርፍ እየሰራ ያለውን ስራ ለማስተዋወቅ በጋራ ይሰራሉ ነው ያሉት ዋና ስራ አስፈጻሚው።
ኢዜአ በ2022 ዓ.ም በአፍሪካ ቀዳሚ የመረጃ ምንጭ ለመሆን ግብ አስቀምጦ በመስራት ላይ እንደሚገኝም አመልክተዋል።
የአዳማ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዘዳንት ዶክተር ለሚ ጉታ በበኩላቸው ስምምነቱ ሁለቱ ተቋማት በአቅም ግንባታ፣በጋራ ፕሮጀክት ቀረጻና ትግበራ፣በሚዲያ አገልግሎትና ሽፋን፣ኮንፈረንሶች ለማዘጋጀትና የምርምር ስራዎችን በጋራ መስራት የሚያስችላቸው ነው ብለዋል።
የመግባቢያ ሰነዱን ወደ ተግባር ለመቀየር ኢዜአ ከዩንቨርስቲው የኢንፎርሜሽን፣ ኮምዩኒኬሽንና ቴክኖሎጂ ቡድን ጋር ፕሮጀክት በመቅረጽ በጋራ መስራት መጀመሩን ጠቁመዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት እና የሕገ መንግስትና ፌደራሊዝም አስተምህሮ ማዕከል በጋራ ለመስራት የሚያስችላቸውን ስምምነት ትናንት መፈራረማቸው የሚታወስ ነው።