የዩኒቨርሲቲው የጋዜጠኝነትና ስነ ተግባቦት ትምህርት ቤት የጥናትና ምርምር ስራዎች ላይ በትኩረት እንዲሰራ ተጠየቀ - ኢዜአ አማርኛ
የዩኒቨርሲቲው የጋዜጠኝነትና ስነ ተግባቦት ትምህርት ቤት የጥናትና ምርምር ስራዎች ላይ በትኩረት እንዲሰራ ተጠየቀ
መስከረም 5/2015/ኢዜአ/ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የጋዜጠኝነትና ስነ ተግባቦት ትምህርት ቤት ለፖሊሲ ግብአት የሚሆኑ የጥናትና ምርምር ስራዎች ላይ ትኩረት በማድረግ እንዲሰራ ተጠየቀ።
የጋዜጠኝነትና ስነ ተግባቦት ትምህርት ቤቱ 25ኛ ዓመት በዓሉን አስመልክቶ የማጠቃለያ መርሃ ግብር እያካሄደ ነው።
በመርሃ ግብሩ ላይ የተገኙት የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር መሀመድ እድሪስ፤ ትምህርት ቤቱ በተለይም ለፖሊሲ ግብአት የሚሆኑ የጥናትና ምርምር ስራዎች ላይ ትኩረት በማድረግ ሊሰራ ይገባል ብለዋል።
የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የጋዜጠኝነት ትምህርት ቤት በሚዲያው ዘርፍ በርካታ አንጋፋ ባለሙያዎችን ያፈራ መሆኑን ጠቅሰው የሚዲያዎች አቅም እንዲገነባ ስልጠናን ጨምሮ በሚያከናውናቸው የተለያዩ ተግባራት አመስግነዋል።
ከዚህ ባለፈ ግን ለአገርና ህዝብ የሚጠቅሙ የጥናትና ምርምር ስራዎች ላይ የበለጠ ሊሰራ ይገባል ብለዋል።
በተለይም ሚዲያው እንዴት ይሻሻል፣ ምን ሊሰራ ይገባል በሚለው ጉዳይ ላይ በማተኮር እንዲሰራ ጠይቀዋል።
የጥላቻ ንግግርና ሀሰተኛ መረጃዎች ፈተና በሆነበት በአሁኑ ወቅት እውነታንና ትክክለኛ መረጃን ማድረስ በሚቻልበት ሁኔታ ላይ በማገዝ የድርሻውን መወጣት አለበት ነው ያሉት።
የትምህርት ቤቱ የሂውማኒቲስ ቋንቋዎች ጥናት እና ስነ ተግባቦት ኮሌጅ ዲን ዶክተር አማኑኤል አለማየሁ፤ ትምህርት ቤቱ ባለሙያዎችን ከማፍራት ባለፈ በምርምርና ማህበረሰብ አገልግሎት ላይ የላቀ ሚናውን እየተወጣ መሆኑን ተናግረዋል
በቋንቋ፣ በስነ ጽሁፍና ሌሎችም ዘርፎች ትልቅ አሻራ ማሳረፍ የቻሉ ባለሙያዎችን ማፍራት የቻለ መሆኑንም ጠቁመዋል።