በበጀት ዓመቱ 280 የገጠር ከተሞችና መንደሮች የኤሌክትሪክ አገልግሎት ተጠቃሚ ይሆናሉ - ኢዜአ አማርኛ
በበጀት ዓመቱ 280 የገጠር ከተሞችና መንደሮች የኤሌክትሪክ አገልግሎት ተጠቃሚ ይሆናሉ
አዳማ ኢዜአ መስከረም 05/2015...በተያዘው የበጀት ዓመት 280 የገጠር ከተሞችና መንደሮችን የኤሌክትሪክ አገልግሎት ተጠቃሚ ለማድረግ እየሰራ መሆኑን የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት አስታወቀ።
ከክልሎች የኤሌክትሪክ አገልግሎት ሪጂኖችና አገልግሎት መስጫ ማዕከላት ከተወጣጡ ከ900 በላይ አመራሮችና የስራ ሃላፊዎች በተገኙበት ውይይት እየተደረገ ነው።
በዚሁ ጊዜ የ2015 ዓ.ም ዕቅድ ማስፈፀሚያ ስልቶችና የትኩረት አቅጣጫዎችን ጨምሮ የቀጣይ ሶስት ዓመት ስትራቴጂክ ዕቅድ ላይ እየመከረ ይገኛል።
የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ዋና ስራ አስፈፃሚ ሽፈራው ተሊላ እንደገለፁት በተያዘው በጀት ዓመት 280 የገጠር ከተሞችና መንደሮች የኤሌክትሪክ አገልግሎት ተጠቃሚ ይሆናሉ።
በዚህም አገልግሎቱ 1 ነጥብ 2 ሚሊዮን ደንበኞች ለማፍራት ግብ አስቀምጦ ወደ ስራ መገባቱን ተናግረዋል።
አገልግሎቱ በተጠናቀቀው የበጀት ዓመት 367 ሺህ 466 አዳዲስ ደንበኞችን ማፍራቱን የገለፁት ዋና ስራ አስፈፃሚው በተመሳሳይ 204 የገጠር ከተሞች የኤሌክትሪክ አገልግሎት ተጠቃሚ መሆናቸውን ገልጸዋል።
በበጀት ዓመቱ አገልግሎቱ በበርካታ ችግሮች ውስጥ አልፎ የተሻለ ስኬት ማስመዝገቡንም ጠቅሰዋል።
በሰሜኑ የአገሪቷ ክፍል በአማራና አፋር ክልሎች በደረሰው ጉዳት 1 ነጥብ 2 ቢሊዮን ብር ኪሳራ መድረሱን አስታውሰዋል።
በአካባቢው በተደረገው የጥገና ስራ ተቋማቱ መልሰው ሙሉ በሙሉ ወደ አገልግሎት መግባታቸውን ተናግረዋል።
በ2015 ዓ.ም ከኤሌክትሪክ ሃይል ሽያጭና ከልዩ ልዩ አገልግሎቶች 43 ነጥብ 1 ቢሊዮን ብር ገቢ ለማግኘት ማቀዱንም አመልክቷል።
የመድረኩ ዓላማ በየደረጃው ያሉ አመራሮችና ሠራተኞች የማስፈፀሚያ አቅም በማጎልበት፣ የደንበኞች የአገልግሎት እርካታን ለማረጋገጥና የተቋሙን ገቢ ለማሳደግ ያለመ ነው ብለዋል።
በተጨማሪም የሃይል ሽያጭ ለማሳደግ፣ የቴክኖሎጂ አጠቃቀም ማሻሻልና ብልሹ አሰራሮችን ለማስወገድ ጭምር መሆኑን ጠቅሰዋል ።
መድረኩ ለቀጣይ ተከታታይ ሶስት ቀናት የሚቆይ መሆኑንም ከወጣው መርሃግብር ማወቅ ተችሏል ።