አምባሳደር ስለሺ በቀለ በሕዳሴ ግድብ የሦስትዮሽ ድርድርንና በተለያዩ ጉዳዮች ዙርያ ከተመድ የአካባቢ ጥበቃ ፕሮግራም ዋና ዳይሬክተር ጋር ተወያዩ - ኢዜአ አማርኛ
አምባሳደር ስለሺ በቀለ በሕዳሴ ግድብ የሦስትዮሽ ድርድርንና በተለያዩ ጉዳዮች ዙርያ ከተመድ የአካባቢ ጥበቃ ፕሮግራም ዋና ዳይሬክተር ጋር ተወያዩ
መስከረም 5 2015 (ኢዜአ) በአሜሪካ የኢትዮጵያ አምባሳደር ስለሺ በቀለ የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የሶስትዮሽ ድርድርን ጨምሮ በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ከተባበሩት መንግስታት ድርጅት የአካባቢ ጥበቃ ፕሮግራም ዋና ዳይሬክተር ኢንገር አንደርሰን ጋር ተወያይተዋል።
አምባሳደር ስለሺ ከዋና ዳይሬክተሯና ከተመድ ረዳት ዋና ፀሐፊ ጋር የግድቡ ግንባታና ድርድሩ አሁን ያለበት ደረጃ፣ ዘላቂ ልማት፣ ትብብርና የናይል ወንዝ አስመልክቶ መምከራቸውን ገልጸዋል።
በሌላ በኩል አምባሳደሩ ከአሜሪካ የኮንግረስ አባል ሀሮልድ ዳላስ ሮጀርስ(ኬንታኪ) ጋር ውይይት ማድረጋቸውን አመልክተዋል።
ለሕግ አውጪ ምክር ቤት አባል ኢ-ፍትሐዊ በሆነው ‘ኢትዮጵያ ስታብላይዜሽን ፒስ ኤንድ ዴሞክራሲ አክት’ ወይም ኤችአር 6600 ረቂቅ ሕግ ላይ መምከራቸውን ተናግረዋል።
የአፍሪካ የእድገትና ዕድል ድንጋጌ(አጎዋ) ተጠቃሚነትን በተመለከተና አሸባሪው ሕወሓት የከፈተው ጦርነትና በኢትዮጵያ ላይ እየፈጸመ ያለውን የሽብር ተግባር ዙርያ ገለጻ ማድረጋቸውን ተናግረዋል።
አሜሪካ በሕጋዊ ምርጫ ስልጣን ለያዘው ከኢትዮጵያ መንግስት ጎን እንድትቆምና ድጋፍ እንድታደርግ ጥሪ ማቅረባቸውን ነው አምባሳደር ስለሺ በትዊተር ገጻቸው ባሰፈሩት መረጃ የገለጹት።
የ84 ዓመቱ ሀሮልድ ዳላስ ሮጀርስ እስካሁን በአሜሪካ ኮንግረስ ለ41 ዓመት አባል በመሆን በሕግ አውጪ ምክር ቤቱ ለረጅም ጊዜ ያገለገሉ ፖለቲከኛና የሕግ ባለሙያ ናቸው።