አሸባሪው ህወሓት በትግራይ ህዝብ ላይ የፈጠረው ጭካኔና ሰቆቃ ሁሉንም ኢትዮጵያዊ እያሳመመ ይገኛል -ኡስታዝ ካሚል ሸምሱ - ኢዜአ አማርኛ
አሸባሪው ህወሓት በትግራይ ህዝብ ላይ የፈጠረው ጭካኔና ሰቆቃ ሁሉንም ኢትዮጵያዊ እያሳመመ ይገኛል -ኡስታዝ ካሚል ሸምሱ
መስከረም 05 ቀን 2015(ኢዜአ) አሸባሪው ህወሓት ሰብአዊ ድጋፍን ለጦርነት በማዋል በትግራይ ህዝብ ላይ የፈጠረው ጭካኔና ሰቆቃ ሁሉንም ኢትዮጵያዊ እያሳመመ ይገኛል ሲሉ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል የሆኑት ኡስታዝ ካሚል ሸምሱ ገለፁ።
ኡስታዝ ካሚል ለአልጀዚራ ቴሌቪዝን እንዳብራሩት በሰሜን ኢትዮጵያ የተፈጠረው ችግር እንዲቀረፍ ካስፈለገ በተቃራኒ ያለው ቡድንም ለሰላማዊ መፍትሄው ራሱን ሊያዘጋጅ ይገባል።
ከአንድ አመት በፊት በኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት ላይ የተፈጸመውን ጥቃት ተከትሎ የነበረው ጦርነት፣ ሰብአዊ ድጋፍ እንዲፋጠን በሚል በኢትዮጵያ መንግስት ተናጥላዊ የተኩስ ማቆም ውሳኔ ቢደረግም በአሸባሪው ህወሃት ጦረኝነት ምክንያት ሊዘልቅ አለመቻሉን ገልጸዋል።
ዘላቂ ሰላምን ለማስፈን መንግስት ተናጥላዊ ተኩስ ማቆም ማካሄዱን፣ ለሰብአዊ ድጋፍ ስርጭቱ ምቹ ሁኔታዎችን መፍጠር ላይ ሲሰራ መቆየቱን አስታውሰዋል።
መንግስት የሰላም አማራጭን በመዘርጋት ከፍተኛ የመንግስት የስራ ሃላፊዎች ያሉበት ቡድን በማዋቀር በየትኛውም ቦታና ሁኔታ የሰላም አማራጩ ሊደረግ እንደሚችል መወሰኑን አንስተዋል።
ኡስታዝ ካሚል የኢትዮጵያ መንግስት ለሰላማዊ አማራጩ ያለውን ዝግጁነት ቀደም ብሎ ለህዝብና ለአለም አቀፉ ማህበረሰብ ማሳወቁን አብራርተው በኢትዮጵያ ውስጥ ያለው አንድ ብሄራዊ መንግስት አንድ የመከላከያ ሃይል እንዲሁም የክልል አስተዳደሮች የመሆናቸው ጉዳይ ህገመንግስታዊ መሆኑ ጥያቄ ውስጥ አይገባም ብለዋል።
በአሸባሪው ህወሃት በኩል የኢትዮጵያን ሉአላዊነትና የግዛት አንድነት የሚፈታተኑ በርካታ ቅድመሁኔታዎችን በመደርደር ንግግር ያለማድረግ ጥረት መኖሩን ያብራሩት ኡስታዝ ካሚል የኢትዮጵያ መንግስት አሁንም የሰላም አማራጩን ተግባራዊ ለማድረግ ዝግጁ መሆኑን አስረድተዋል።