አሸባሪው ህወሃት በሐሰት ፕሮፓጋንዳ የተካነ አደናጋሪ ባህሪ የተላበሰ ቡድን መሆኑን የዓለም ዓቀፉ ማህበረሰብ መረዳት ይኖርበታል - አምባሳደር ደሴ ዳልኬ - ኢዜአ አማርኛ
አሸባሪው ህወሃት በሐሰት ፕሮፓጋንዳ የተካነ አደናጋሪ ባህሪ የተላበሰ ቡድን መሆኑን የዓለም ዓቀፉ ማህበረሰብ መረዳት ይኖርበታል - አምባሳደር ደሴ ዳልኬ
መስከረም 05 ቀን 2015 (ኢዜአ) አሸባሪው ህወሃት በሐሰት ፕሮፓጋንዳ የተካነ አደናጋሪ ባህሪ የተላበሰ ቡድን መሆኑን የዓለም ዓቀፉ ማህበረሰብ መረዳት ይኖርበታል ሲሉ በኮሪያ ሪፐብሊክ የኢትዮጵያ ባለሙሉ ስልጣን አምባሳደር ደሴ ዳልኬ ገለጹ።
በሰሜን ኢትዮጵያ ቡድኑ የፈጠረውን ችግር ለመፍታት መንግስት እየተከተለ ያለውን የሰላም አማራጭ የአለም አቀፉ ማህበረሰብ መደገፍ እንዳለበት ገልጸው፤ ኮሪያ ሪፐብሊክም የድርሻዋን እንድትወጣ ጠይቀዋል።
ከደቡብ ኮሪያው ኮሪያ ታይምስ ጋር ቆይታ ያደረጉት አምባሳደር ደሴ የኢትዮጵያ ወቅታዊ ሁኔታን በተመለከተ ሰፊ ገለጻ አድርገዋል።
ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ የህወሃት የሽብር ቡድንን የአደናጋሪነት ባህሪ ሊገነዘብ ይገባል በማለት ገልጸው፤ የሽብር ቡድኑን ተለዋዋጭ ባህሪ በውል መገንዘብ እንደሚገባ አስረድተዋል።
ቡድኑ በኢትዮጵያ የመጣውን ለውጥ ባለመቀበል የጦረኝነት ባህሪውን በመጠቀም የፌዴራል መንግስትን ሲተናኮስ መቆየቱን አስታውሰው፤ በአገር መከላከያ ሰራዊት ላይ ጥቃት በመፈጸም ጦርነት መለኮሱን ገልጸዋል።
ይህ ብቻ ሳይሆን መንግስት ለሰላም መስፈን የሚወስዳቸውን እርምጃዎች ሲያደናቅፍ መቆየቱን ተናግረዋል።
ቡድኑ ተደጋጋሚ ትንኮሳ መፈጸሙን ገልጸው፤ ጦርነት በመለኮስ ወደከፋ ጥፋት በመሸጋገሩ መንግስት ሀገሪቱን የመጠበቅ ግዴታ ስላለበት የመከላከል ስራ እየሰራ እንደሚገኝም አንስተዋል፡፡
መንግስት ችግሩ በሰላማዊ መንገድ እንዲቋጭ በአፍሪካ ህብረት በኩል የሰላም አማራጭ ሂደትን እየተከተለ መሆኑን አመልክተዋል።
የሰብዓዊነት የተኩስ ማቆም ውሳኔ መወሰንና የሰላም አማራጭ ኮሚቴ አቋቁሞ ሰላምን ለማረጋገጥ መንግስት ብዙ ርቀት መጓዙን ገልጸዋል።
የፌዴራል መንግስት ለሰላማዊ ውይይቱ ያለውን ቁርጠኝነት ቢያሳይም የሽብር ቡድኑ ግን በህዝብ ማዕበል 3ኛ ዙር ወረራ እና ግፍ መፈጸም መጀመሩን አብራርተዋል፡፡
የሽብር ቡድኑ የተሳሳቱ መረጃዎችን በማሰራጨት የዓለም አቀፍ ማህበረሰቡን ማሳሳት፣ የትግራይ ክልል ነዋሪዎችን በማፈን ወጣቶችን በማስገደድ በህዝብ ማዕበል በመጠቀም ወደ ጦርነት ቀጣና ማሰማራትን ስራዬ ብሎ ተያይዞታል ብለዋል፡፡
የሽብር ቡድኑ ለህዝብ እንደማያስብ ከሚጠቁሙ ማሳያዎች መካካል አንዱ እና ዋነኛው ለተቸገረው ህዝብ መቅረብ ያለባቸውን እንደ ምግብ እና ነዳጅ አቅርቦቶች እንዳይቀርቡ ጦርነት በመክፈት ጭምር እንቅፋት መሆኑን አንስተዋል፡፡
የኢትዮጵያ መንግስት ጉዳዩ በሰላማዊ መንገድ እንዲፈታ ፍላጎት ያለው መሆኑን በመረዳት ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ መንግስት በሚያደርገው ጥረት ላይ አስፈላጊውን ድጋፍ ማድረግ አለበት ብለዋል፡፡