የሀይማኖት ተቋማት ኮቪድ -19ኝን በመከላከሉ ተግባር የግንዛቤ ስራዎችን አጠናክረው መቀጠል አለባቸው-ጤና ሚኒስቴር - ኢዜአ አማርኛ
የሀይማኖት ተቋማት ኮቪድ -19ኝን በመከላከሉ ተግባር የግንዛቤ ስራዎችን አጠናክረው መቀጠል አለባቸው-ጤና ሚኒስቴር
ሀዋሳ መስከረም 04/2015 (ኢዜአ)የሀይማኖት ተቋማት ኮቪድ 19ኝን ለመከላከል በሚከናወኑ ተግባራት ዙሪያ የህዝቡን ግንዛቤ የማሳደግና የማስተማር ስራቸውን አጠናክረው መቀጠል እንዳለባቸው የጤና ሚንስቴር አሳሰበ ።
በኮቪድ 19 ዙሪያ የሚመክር መድረክ በሀዋሳ እየተካሄደ ነው።
በምክክር መድረኩ ላይ የጤና ሚንስትሯ ዶክተር ሊያ ታደሰ እንዳሉት ባለፉት ዓመታት በሀገራችን ኮቪድን ጨምሮ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጫና የሚያሳድሩ የጤና ችግሮችን ለመፍታት ከተለያዩ አካላት ጋር በቅንጅት ሲሰራ ቆይቷል።
በተለይ የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ በዓለም አቀፍ ደረጃ ከተከሰተበት ጊዜ አንስቶ እስካሁን በሽታውን ለመከላከል ከኢትዮጵያ ሀይማኖት ተቋማት ጉባኤ ጋር በጋራ ሲሰራ እንደቆየ አስታውሰዋል።
"በተሰራው ስራም ውጤት ተገኝቶበታል" ያሉት ሚንስትሯ የመተላለፊያ መንገዶችን በመለየት ህዝቡን በማስተማርና መከላከያ መንገዶችን እንዲተገብር ግንዛቤ በማሳደግ በኩል የሀይማኖት ተቋማት ሚና የላቀ እንደነበር አስታውሰዋል።
“በተለይ ከክትባቱ ጋር ተያይዞ ይሰራጩ በነበሩ አሉባልታዎች ዙሪያ የሀይማኖት ተቋማት ተከታዮቻቸውን በማስተማርና በማስተባበር ጭምር ክትባቱን እንዲከተቡ ያደረጉበት መንገድ ውጤት ያስገኘ ነው” ብለዋል።
በዕምነት ተቋማት እገዛና ድጋፍ ጭምር እንደ ሀገር 43 ነጥብ 1 ሚሊዮን ሰዎች ቢያንስ አንድ ዙር ክትባት መከተባቸውን ጠቁመው ከተከተቡት ውስጥ 36 ነጥብ 6 ሚሊዮን የሚሆኑት ሙሉውን ክትባት የወሰዱ መሆኑን ተናግረዋል።
ኮቪድ የዜጎችን ህይወት በማመሰቃቀልና ለከፋ አደጋ በመዳረግ ክፉ ከሚባሉ በሽታዎች መካከል የሚጠቀስ መሆኑን የገለጹት ሚንስትሯ አሁን ላይ እየታየ ያለው መዘናጋት ስጋት እየፈጠረ በመሆኑ የሀይማኖት ተቋማት የመከላከል ስራዎች ላይ አትኩረው እንዲቀጥሉ አሳስበዋል ።
ቫይረሱ ከተከሰተበት ጊዜ አንስቶ በሀገራችን 493 ሺህ ሰዎች መያዛቸውንና 7 ሺህ 572 ሰዎች ህይወታቸውን እንዳጡ ጠቁመዋል።
"ከዚህ ባለፈ ኤች አይ ቪ/ኤድስና ወባ አሁንም ያልተሻገርናቸው ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጫና እያሳረፉ ያሉ ተላላፊ በሽታዎች በመሆናቸው በአትኩሮት ተቀናጅተን መስራት ይገባናል" ሲሉ ጠቁመዋል።
ባለፈው ዓመት ብቻ ኤች አይ ቪ ምርመራ ከተደረገላቸው ውስጥ ከ20 ሺህ የሚበልጡ አዲስ ሰዎች ቫይረሱ አንደተገኘባቸው ለአብነት ጠቅሰዋል ።
ሚንስትሯ አያይዘው "የአየር ንብረት ለውጡን ተከትሎም የወባ ስርጭት እየጨመረ በመምጣቱ ሁላችንም ርብርብ ልናደርግ ይገባል” ብለዋል።
የኢትዮጵያ ሀይማኖት ተቋማት ጉባኤ ጠቅላይ ጸሀፊ ሊቀ ትጉሀን ቀሲስ ታጋይ ታደለ በበኩላቸው እንዳሉት የኮቪድ ስርጭትን ለመከላከል በተከናወነው ተግባር ውስጥ ጉባኤው የሀይማኖት ተቋማትን በማስተባበር ሲሰራ ቆይቷል።
ከጤና ሚንስቴርና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር በመሆን የተሰራው ስራ በርካታ ተግዳሮቶችን በማለፍ ስኬታማ እንደነበር አስታውሰው አሁንም የሚስተዋሉ ክፍተቶች እንዳሉ ጠቁመዋል።
የዕምነት ተቋማትና አባቶች የሀይማኖቱ ስርዓት በሚያዘው መንገድ ተከታዮቻቸውን በማስተማር ክትባቱንም እንዲከተቡ በማስተባበር ጭምር በርካቶች እንዲከተቡ ማድረግ እንደተቻለ ገልጸዋል።
“ከኮቪድ ባለፈ ኤች አይ ቪና ወባ እስካልተወገዱ ድረስ የሀገርም የዓለምም ችግሮች በመሆናቸው የዕምነት ተቋማት በመከላከያ መንገዶች ዙሪያ ለተከታዮቻቸው ትምህርት በመስጠት ለውጥ እንዲመጣ ማገዝ አለባቸው” ብለዋል።
የሲዳማ ክልል ጤና ቢሮ ሀላፊ ዶክተር ሰላማዊት መንገሻ በበኩላቸው በክልሉ የኮሮና ቫይረስ ስርጨትን ለመግታት የተከናወነው ተግባር ወረርሽኙ የከፋ ጉዳት እንዳያደርስ ያስቻለ ቢሆንም አሁንም ቀሪ ተግባራት እንዳሉ ገልጸዋል።
የመከላከያ ክትባቱን መስጠት ከተጀመረበት ጊዜ አንስቶ በክልሉ ዕድሜያቸው 12 ዓመትና ከዛ በላይ የሆናቸው ከ2 ሚሊዮን በላይ ሰዎች መከተባቸውን ተናግረዋል።
ለሁለት ቀናት በሚቆየው በምክክር መድረክ ላይ የሀይማኖት ተቋማት መሪዎች፣ ጤና ባለሙያዎችና የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት እየተሳተፉ ነው ።