ቀጥታ፡

ለመከላከያ ሰራዊት የምናደርገውን ድጋፍ አጠናክረን እንቀጥላለን - በገንዳ ውሃ ከተማ ነዋሪዎች

መተማ ፤ መስከረም 4/2014(ኢዜአ) ለመከላከያ ሰራዊትና ሌሎች የፀጥታ ሃይሎች በስንቅ ከሚያደርጉት ዕገዛ ባሻገር ግንባር ድረስ በመዝመት ድጋፋቸውን አጠናከረው ለመቀጠል ቁርጠኛ መሆናቸውን በምዕራብ ጎንደር ዞን የገንዳውሃ ከተማ ነዋሪዎች ተናገሩ።

የምዕራብ ጎንደር  ህዝብ የሽብር ቡድኑ የከፈተውን  ሶስተኛ ዙር ጦርነት  ለመመከት የሚያግዝ ከ3 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት የዓይነት ድጋፍ ማድረጉን  የዞኑ  አስተዳደር ሎጅስቲክ አሰባሳቢ ኮሚቴ አስታውቋል።

የገንዳውሃ ከተማ ነዋሪ  ወይዘሮ አንችናሉ ፀጋው ፤  የሽብር ቡድኑ ከታሪካዊ የኢትዮጵያ  ጠላቶች ጋር በማበር  ህዝቦቿን ለማዋረድና ሀገሪቱን ለማፍረስ  ሲጥር መቆየቱን አንስተዋል።

ለዚህም የሰሜን ዕዝን ከጀርባ ከመውጋት ጀምሮ ወደ አማራና አፋር ክልሎች ተደጋጋሚ ወረራ በማካሄድ ንጹሃንን ገድሏል፣ አካል አጉድሏል፣ ሃብትና ንብረት ዘርፏል አውድሟል ሲሉ አውስተዋል።

ሆኖም  የሽብር ቡድንም ሆነ ታሪካዊ ጠላቶቻችን ማወቅ ያለባቸው  ኢትዮጵያ በጀግኖች ልጆቿ ደምና አጥንት ለዘላለም ተከብራ የምትኖር ሃገር መሆኗን ነው ብለዋል።

እኛም በግንባር ጠላትን ለሚፋለመው ሰራዊቱ  ስንቅና ሌሎች ቁሳቁሶችን በማቅረብ በደጀንነት ከማገዝ ባሻገር ግንባር ድረስ በመዝመት ለመደገፍ   እንደወትሮ ሁሉ አሁንም ቁርጠኛ መሆናቸውን ተናግረዋል።

አቶ መሐመድ ኢብራሂም በበኩላቸው፤ በአከባቢያቸው ገንዘብ በማዋጣት ለእርድ የሚሆኑ ሰባት ፍየሎችን ለሎጂስቲክ ኮሚቴው ማስረከባቸውን ገልጸዋል።

"ይህ የደጀንነት ተግባር የሽብር ቡደኑ ተወግዶ ሀገራችን ሰላም እስክትሆን ድረስ የሚቀጥል ነው" ያሉት ነዋሪው፤  ለድጋፉ የአካባቢያቸውን ማህበረሰብ በማስተባበር የድርሻቸውን እየተወጡ መሆኑን አስታውቀዋል።

ከገንዘብ ድጋፍ በተጨማሪም ከመከላከያና ሌሎች የጸጥታ ሃይሎች ጎን በመሰለፍ ለሀገራቸው ሰላምና ክብር የድርሻቸውን ለመወጣት ቁርጠኛ እንደሆኑ  ተናግረዋል።

"ለሰራዊቱ  ምግብ ብቻ ሳይሆን አልባሳትና ደም በመለገስ ከጎናቸው መሆናቸውን ማረጋገጥ ይገባናል" ያሉት ደግሞ  ወይዘሮ አትጠገብ አስናቀው ናቸው።

ታናሽ ወንድማቸው ከመከላከያ ሰራዊት  ጋር ተሰልፎ አሸባሪው ህውሃትን በመዋጋት ላይ መሆኑን ጠቅሰው፤ ልጃቸውም ወደ ግንባር ለመዝመት መዘጋጀቱን ጠቁመዋል።

የዞኑ አስተዳደር የሎጅስቲክ አሰባሳቢ ኮሚቴ አስተባባሪ አቶ ደረሰ አዱኛ፤  ባለሃብቶች ጨምሮ የዞኑ ነዋሪዎች የሽብር ቡድኑ የከፈተውን ጦርነት  ለመመከት የሚያግዝ ከ3ሚሊዮን በላይ የሚገመት ድጋፍ  ማድረጋቸውን አስታውቀዋል።

ከተደረገው ድጋፍም ለእርድ የሚውሉ በሬዎችና  ፍየሎች፣ የምግብና ሌሎች ቁሶች እንደሚገኙበት አስረድተዋል።

የምዕራብ ጎንደር ዞን ህዝብ ባለፈው ዓመት በነበረው የህልውና ዘመቻ 100ሚሊዮን ብር የሚጠጋ የጥሬ ገንዘብና የዓይነት ድጋፍ አድርጓል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም