ቅንጅት በቡራዩና አካባቢዋ በደረሰው ጥቃት የተሰማውን ሃዘን ገለጸ - ኢዜአ አማርኛ
ቅንጅት በቡራዩና አካባቢዋ በደረሰው ጥቃት የተሰማውን ሃዘን ገለጸ
አዲስ አበባ መስከረም 9/2011 ቅንጅት ለአንድነትና ለዲሞክራሲ (ቅንጅት) በቡራዩና አካባቢው በተፈጸመው ጥቃት የተሰማውን ሃዘን ገልጿል። በቡራዩና አካባቢዋ ለደረሰው የሰው ህይወት መጥፋት፣ ለአካል ጉዳትና ከቤት ንብረት መፈናቀል ምክንያት የሆኑ አካላት ለህግ እንዲቀርቡም ጠይቋል። ቅንጅት ለኢዜአ በላከው መግለጫ፤ አገሪቱ ዜጎች የተከበሩባት፣ የዴሞክራሲ ስርዓት የሰፈነባትና የበለጸገች እንድትሆን ትግሉን እንደሚያጠናክር ገልጿል። ገዢው ፓርቲ የኢትዮጵያ ህዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ግንባር (ኢህአዴግ) ፖለቲካዊ፣ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ለውጦችን ለማምጣት እንቅስቃሴ ላይ ቢሆንም የህግ የበላይነት ለማስፈን መስራት እንዳለበት አመልክቷል። በተለይም ከጊዜ ወደ ጊዜ በአገሪቱ በሚፈጠሩ ግጭቶች ምክንያት የዜጎች ህይወት አደጋ ላይ መሆኑን ተከትሎ ተፎካካሪ ፓርቲዎች ሁሉን አቀፍ ለውጥ ይመጣ ዘንድ በትኩረት እንዲሰሩ ጥሪ አስተላልፏል። በተፈጸመው ጥቃት ጉዳት ለደረሰባቸው ቤተሰቦች መጽናናትን ተመኝቷል።