ቀጥታ፡

አለም አቀፉ ማህበረሰብ አሸባሪው ሕወሓት የጀመረውን ጦርነት አቁሞ ለሰላም ውይይት እንዲቀመጥ ጫና ሊያደርግ ይገባል-አምባሳደር ተፈሪ መለሰ

መስከረም 4 ቀን 2015 (ኢዜአ) አለም አቀፉ ማህበረሰብ አሸባሪው ሕወሓት የጀመረውን ጦርነት አቁሞ ለሰላም ውይይት እንዲቀመጥ ጫና ሊያደርግ ይገባል ሲሉ በእንግሊዝ የኢትዮጵያ አምባሳደር ተፈሪ መለሰ ገለጹ።

አምባሳደሩ አልጀዚራ ድረ ገጽ ላይ ባሰፈሩት ጽሑፍ እንዳሉት አለምአቀፉ ማህበረሰብ አሸባሪ ቡድኑ ከጀመረው የጥፋት መንገድ እንዲመለስ ጫና ሊያደርግ ይገባል።

አሸባሪው ሕወሓት በአፍሪካ ሕብረት ጥላ ስር ለሚደረገው የሰላም ውይይት ፍላጎት መግለጹን ያስታወሱት አምባሳደሩ፤ በተናገረው ቃል እንዲጸና አለምአፉ ማህበረሰብ ሚናውን ሊወጣ ይገባል ነው ያሉት።

የኢትዮጵያ መንግስት በየትኛውም ግዜና ቦታ የሰላም ውይይት ለማድረግ ዝግጁ መሆኑን የገለጹት አምባሳደሩ አሸባሪው ሕወሓት ግን የሰላምን ጥሪ ወደ ጎን በመተው በአሁኑ ግዜም ጦርነት መክፈቱን አመላክተዋል።

አሸባሪው ቡድን በተደጋጋሚው እንደሚታየው በምንም አይነት ሁኔታ ለቃሉ የማይታመን በመሆኑ አለም አቀፉ ማህበረሰብ ቡድኑ ላይ ጫና ማድረግ መጀመር አለበት ብለዋል።

አሸባሪው ሕወሓት ሲያደርግ የቆየውን አሰቃቂ የጦር ወንጀሎች፣ንጹሃንን መግድል፣ለእርዳታ የተላኩ ቁሳቁሶችን መዝረፍ፣የህዝብ ሃብት ማውደም እና ለሌሎች ወንጀሎቹ ማስረጃዎች መኖራቸውን ገልጸዋል።

ከዚህ በኋላ ሌላ ዙር ጦርነት ማንንም አይጠቅምም ያሉት አምባሳደሩ በተለይ ከስድስት ሚሊዮን በላይ ለሚገመተው የትግራይ ህዝብ አሸባሪው ቡድን የሚያደርሰው ሰቆቃ ሊያበቃ ይገባል ብለዋል።

በመሆኑም የኢትዮጵያ መንግስት ለሰላም እና ለአንድነት ቅድሚያ የሚሰጥ መሆኑን ያስገነዘቡት አምባሳደር ተፈሪ የሀገሪቱን ሉአላዊነት እና የህዝቡን ሰላም የመጠበቅ ሀላፊነቱን በአግባቡ ይወጣል ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም