የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት እና የሕገ መንግስትና ፌደራሊዝም አስተምህሮ ማዕከል በጋራ ለመስራት ተስማሙ - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት እና የሕገ መንግስትና ፌደራሊዝም አስተምህሮ ማዕከል በጋራ ለመስራት ተስማሙ
መስከረም 4 ቀን 2015(ኢዜአ) የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት እና የሕገ መንግስትና ፌደራሊዝም አስተምህሮ ማዕከል በጋራ ለመስራት የሚያስችላቸውን ስምምነት ተፈራረሙ።
ስምምነቱን የማዕከሉ ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ኃይለየሱስ ታዬ እና የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ሰይፈ ደርቤ ዛሬ በአዲስ አበባ ተፈራርመዋል።
የሕገ መንግስትና ፌደሬሊዝም አስተምህሮ ማዕከል በ2011 ዓ.ም የተቋቋመ ሲሆን ተጠሪነቱም ለፌደሬሽን ምክር ቤት ነው፡፡
ዓላማውም በኢትዮጵያ ሕገ መንግስትና በፌደራሊዝም ዙሪያ ያለውን ግንዛቤ ለማሳደግ ሲሆን በዚሁ መሰረት ስልጠናዎችን በመስጠት ላይ ነው።
የማዕከሉ ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ኃይለየሱስ በዚሁ ወቅት፤ የአንድ አገር እድገት የሚረጋገጠው ዜጎች በመሰረታዊ የህግ ጉዳዮች ላይ በቂ ግንዛቤ ሲኖራቸውን መሆኑንም አንስተዋል።
ዜጎች መብትና ግዴታቸውን እንዲሁም አገር የምትመራበትን ስርዓት መገንዘብ እንዳለባቸው ጠቁመው የአንድ አገር የዲሞክራሲ ስርዓትም የሚገነባው በዚሁ መንገድ ነው ብለዋል።
ማዕከሉ ከዚህ አኳያ የተቋቋመበትን ዓላማ በማሳካት ረገድ ከኢዜአ ጋር ያደረገው ስምምነት ወሳኝ መሆኑን ነው የገለጹት።
"የሰው አስተሳሰብ ካልተስተካከለ ወርቃማ ሕግ ቢዘጋጅም ትርጉም የለውም" ያሉት ዶክተር ኃይለየሱስ በአስተሳሰብ ቀረጻ ላይ ከኢዜአ ጋር መስራት በመቻላችን ደስተኞች ነን ብለዋል።
ኢትዮጵያ ውስጥ አስተሳሰብና አመለካከት ላይ መስራት የብዙ ችግሮች መፍቻ ቁልፍ መሆኑን ጠቁመው ማዕከሉ በዚሁ ማዕቀፍ ውስጥ እየተንቀሳቀሰ መሆኑን አስረድተዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ሰይፈ ደርቤ በበኩላቸው ማዕከሉ በህዝቦች ዘንድ አንድነትን ለማስፈን የሚሰራ ተቋም ከመሆኑ አኳያ አብረን መስራት በመቻላችን ደስተኞች ነን ነው ያሉት።
ማዕከሉ ሊያሳካ ያቀዳቸው ዓላማዎች እውን እንዲሆኑ ኢዜአ በቁርጠኝነት ለመስራት ዝግጁ መሆኑንም አረጋግጠዋል።
በተለይም በአዲሱ ዓመት የሰላምና የለውጥ ተስፋዎችን ለማሳካት ስምምነቱ ተጨማሪ አቅም እንደሚሆንም ነው ዋና ስራ አስፈጻሚው ያብራሩት።