ቀጥታ፡

የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤትና በስሩ ያሉ 18 ተጠሪ ተቋማት ለሀገር መከላከያ ሠራዊት ከ90 ሚሊዮን ብር በላይ የገንዘብና የአይነት ድጋፍ አደረጉ

መስከረም 4/2015/ኢዜአ/ የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤትና በስሩ ያሉ 18 ተጠሪ ተቋማት ለሀገር መከላከያ ሠራዊት ከ90 ሚሊዮን ብር በላይ የገንዘብና የአይነት ድጋፍ አደረጉ

በተመሳሳይ የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል ከዳውሮ እና ኮንታ ዞን ሕዝብ ያሰባሰበውን 361 ሰንጋዎች፣ 33 በግ አና ፍየል በአጠቃላይ ከ26 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት ድጋፍ አድርጓል።

የኢትዮጵያ ነዳጅ አቅራቢ ድርጅት ደግሞ ከ2 ሚሊዮን ብር በላይ ድጋፍ ያደረገ ሲሆን በአጠቃላይ በዛሬው እለት ለሀገር መከላከያ ሠራዊት ከ118 ሚሊዮን ብር በላይ የገንዘብ እና የዓይነት ድጋፍ ተደርጓል።

በጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤትየአገልግሎትና መልካም አስተዳደር ሚኒስትርዴኤታ ወይዘሮ አለምጸሐይ ጳውሎስ የጽህፈት ቤቱ ሰራተኞችና ተጠሪ ተቋማት ለጀግናው የሀገር መከላከያ ሠራዊት ከዚህ ቀደምም ድጋፍ ሲያደርጉ መቆየታቸውን አስታውሰዋል።

አሁንም ሕይወቱን ሰውቶ የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት እያስከበረ ለሚገኘው ሠራዊት የሚያደርጉትን ሁለንተናዊ ድጋፍ አጠናክረው እንደሚቀጥሉም ቃል ገብተዋል።

የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ከዳውሮ እና ኮንታ ዞኖች የሰበሰበውን 26 ሚሊየን ብር የሚያወጣ ድጋፍ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ደረሰ ገቲሳ ለሠራዊቱ አስረክበዋል።

ባለፈው ሳምንት ክልሉ ከከፋ ዞን ያሰባሰበውን ከ24 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት የአይነት ድጋፍ ማስረከቡን ያስታወሱት ኃላፊው፤ ድጋፉ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ነዳጅ አቅራቢ ድርጅት ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ታደሰ ኃይለማርያም በበኩላቸው ድርጅቱ ቀደም ሲል በግንባር እየተዋደቀ ለሚገኘው ሠራዊት ድጋፍ ሲያደረግ መቆየቱን ተናግረዋል።

በዛሬው እለት ከ2 ሚሊዮን ብር በላይ ድጋፍ ያደረገ ሲሆን በቀጣይም ከሠራዊቱ ጎን መቆማችንን እናረጋግጣለን ብለዋል።

የመከላከያ ሚኒስትር ዴኤታዋ ማርታ ሉዊጂ በበኩላቸው የኢትዮጵያ ህዝብ በሁሉም ግንባር ለተሰለፈው የሀገር መከላከያ ሰራዊት ደጀንነቱን በተግባር እያሳየ መሆኑን ተናግረዋል።

እስካሁን ለሠራዊቱ ለተደረገው ድጋፍ አመስግነው በቀጣይም ለኢትዮጵያ ሉዓላዊነት መከበር ሁላችንም በአንድነት በመቆም ድጋፉ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪ አቅርበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም