በድሬዳዋ የዘንድሮ የመማር ማስተማር ስራን ለመጀመር ዝግጅት መደረጉን የትምህርት ቢሮ አስታወቀ

19

ድሬዳዋ ፤ መስከረም 3/2015 (ኢዜአ) በድሬዳዋ አስተዳደር የ2015 የትምህርት ዘመን የመማር ማስተማር ስራን ለማስጀመር በቂ ዝግጅት መደረጉን የአስተዳደሩ የትምህርት ቢሮ አስታወቀ።

በአስተዳደሩ የዘመኑ  ትምህርት መስከረም 9/2015ዓ.ም  እንደሚጀምር ተገልጿል።

የትምህርት ቢሮ  ኃላፊ ወይዘሮ ሙሉካ መሐመድ ፤  የ2015  የትምህርት  ዘመን  የመማር ማስተማር ሂደት ለማስጀመር ኮሚቴ በማዋቀር የቅድመ ዝግጀት ሲደረግ መቆየቱን ለኢዜአ ተናግረዋል።

በዚህም ተማሪዎች ወደ ትምህርት ቤት እንዲመጡ ከገጠር እስከ ከተማ ማህበረሰብ አቀፍ ቅስቀሳ መደረጉን ጠቅሰዋል።

በክረምቱ ወራት ተደራሽነት መሠረት ያደረገ በገጠርና ከተማ ትምህርት ቤቶች ላይ የማስፋፊያ ስራ መከናወኑንም አስረድተዋል።

የመማሪያ ክፍሎችን እድሳት ፣ የመጽሐፍት ህትመት እና ሌሎችም ለመማር  ማስተማር ስራ የሚያገዙ ቁሶች ዝግጅት መጠናቀቁን ተናግረዋል።

በትምህርት ዘመኑ በድሬዳዋ አስተዳደር ከ131 ሺህ በላይ ቅድመ መደበኛና አንደኛ ደረጃ እንዲሁም የሁለተኛ ደረጃ ተማሪዎችን ተቀብሎ ትምህርት ለማስጀመር  መሰናዳታቸውን የቢሮው ኃላፊ  አስታውቀዋል።

በአስተዳደሩ ለሚገኙ  መምህራን ከመስከረም አራት እስከ ሰባት በአዲሱ ትምህርት ሥርዓት ዙሪያ ስልጠና ይሰጣል ብለዋል ኃላፊዋ ።

ተማሪዎች የሚጠበቅባቸውን ቁሳቁስና የሥነ ልቦና ዝግጅት በማድረግ ከመስከረም 9/2015 ዓ.ም ጀምሮ በትምህርት ገበታቸው እንዲገኙ  አሳስበዋል።

ወላጆች ተማሪዎች በተጠቀሰው ቀን ወደ ትምህርት ገበታቸው እንዲሄዱ ድጋፍ እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም