ኢትዮጵያ የሰው ሃብት ልማትን ለማጎልበት በትምህርት ጥራት ላይ መስራት እንዳለባት ተጠቆመ - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ የሰው ሃብት ልማትን ለማጎልበት በትምህርት ጥራት ላይ መስራት እንዳለባት ተጠቆመ

መስከረም 3/2015 (ኢዜአ) ኢትዮጵያ የሰው ሃብት ልማትን ለማጎልበት በትምህርት ጥራት ላይ በትኩረት መስራት እንዳለባት በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሰው ሃብት ልማት እድገት አመላካች ሪፖርት ጠቆመ።
ዓለም አቀፉ የ2021/22 የሰው ሃብት ልማት አመላካች ሪፖርት ዛሬ በአዲስ አበባ ይፋ ሆኗል።
የሩሲያ-ዩክሬን ጦርነት፣ ኮቪድ-19 ወረርሽኝ፣ የዋጋ ግሽበትና መሰል ችግሮች በመኖራቸው በዓለም አገራት የሰው ሃብት ልማት ዕድገት ላይ ተጽዕኖ መፈጠሩ በሪፖርቱ ተመላክቷል።
በኢትዮጵያ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የልማት ፕሮግራም ዳይሬክተር ቱርሃን ሳለህ፤ 90 ከመቶ በላይ የሚሆኑ የዓለም ሀገራት የሰው ሃብት ልማት የእድገት ምጣኔ መቀነሱን አመላካች ሪፖርቱ ማሳየቱን ጠቅሰዋል።
በአንጻሩ ኢትዮጵያ በተፈጥሮና ሰው ሰራሽ ተጽዕኖ ውስጥ ደረጃዋን ማስጠበቋን አድንቀው፤ የሰው ሃብት ልማት እድገትን ለማረጋገጥ የትምህርት ጥራትን ማሻሻል እንዳለባት ነው ተናግረዋል።
በአዲሳ አበባ ዩኒቨርሲቲ የምጣኔ ሃብት ተመራማሪው ፕሮፌሰር አለማየሁ ገዳ፡ ኢትዮጵያ ዓለም አቀፍና የውስጥ ጫናዎች ቢያጋጥሟትም በትምህርትና በጤና ዘርፎች ላይ የተሰሩ ተግባራት የሰው ሃብት ልማት ደረጃዋን እንድታስቀጥል ትልቅ ሚና እንዳላቸው ተናግረዋል።
በቀጣይም በሁሉም የሰው ሃብት የልማት እድገት ማረጋገጫ ዘርፎች ላይ በትኩረት መስራት እንደሚገባም አመላክተዋል።
ኢትዮጵያ የልማት አጀንዳዎቿን እውን ለማድረግ በምታደረገው ጥረት ሁሉ የተባበሩት መንግስታት ድርጀት የተለመደ ድጋፉን አጠናክሮ እንደሚቀጥልም ተጠቁሟል።