የአፍሪካ አገራት የአየር ንብረት ለውጥን ለመቋቋም የሚያስችላቸውን የፋይናንስ አቅም በመፍጠር ረገድ በጋራ ሊሰሩ ይገባል

መስከረም 3/2014/ኢዜአ/ የአፍሪካ አገራት የአየር ንብረት ለውጥን ለመቋቋም የሚያስችላቸውን የፋይናንስ አቅም በመፍጠር ረገድ በጋራ ሊሰሩ እንደሚገባ ተገለጸ።

በአፍሪካ የአየር ንብረት ለውጥን ለመቋቋም የሚያስችል የፋይናንስ ተደራሽነት ላይ ትኩረቱን ያደረገ ውይይት በአዲስ አበባ ተካሂዷል።

የአፍሪካ ልማት ባንክ የአየር ንብረት ለውጥ እና የምስራቅ አፍሪካ አረንጓዴ ልማት አካባቢያዊ ኃላፊ ዶክተር ኦሉፎንሶ ሶሞሪን በዚህ ወቅት አፍሪካ ለአየር ንብረት ለውጥ ያላት አስተዋጽኦ እዚህ ግባ የሚባል ባይሆንም የችግሩ ገፈት ቀማሽ ከሆነች ግን ቆይታለች ነው ያሉት፡፡

በመሆኑም ባንኩ ችግሩን በመከላከል ረገድ የበኩሉን ድርሻ እየተወጣ መሆኑንም ነው የተናገሩት፡፡

በአፍሪካ በቀጣይ አምስት ዓመታት የአየር ንብረት ለውጥን ለመከላከል 25 ቢሊዮን ዶላር ወጪ የሚደረግበት ፕሮጀክት መቀረጹን  ጠቅሰው፤ ከዚህም ውስጥ የአፍሪካ ልማት ባንክ ግማሽ ያህሉን ይሸፍናል ነው ያሉት፡፡

ቀሪው ደግሞ በአፍሪካ አገራት መንግስታትና በሌሎች አጋር አካላት የሚሸፈን እንደሚሆን ነው የጠቀሱት፡፡

ይህም ኢትዮጵያን ጨምሮ በርካታ ታዳጊ አገራትን ተጠቃሚ እንደሚያደርግ ያላቸውን እምነት ገልጸዋል፡፡

የአፍሪካ አገራት የአየር ንብረት የሚያደርሰውን ተጽዕኖ ለመከላከል በጋራ መቆም እንዳለባቸውም ነው ጥሪ ያቀረቡት፡፡

በዚህም በአህጉሩ ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ የሚያስችሉ ስራዎች ተጠናክረውመቀጠል እንዳለባቸውም እንዲሁ፡፡

የኮንራድ አድናዎር ፋውንዴሽን (ካስ) የአፍሪካ ህብረትና የኢትዮጵያ ተወካይ ቤኖ ሙችለር በበኩላቸው የአየር ንብረት ለውጥ በታዳጊ አገራት ከፍተኛ ተጽዕኖ እያስከተለ እንደሚገኝ ገልጸው ይህም ከፋይናንስ አቅርቦት ችግር ጋር የሚያያዝ መሆኑን ገልጸዋል።

ታዳጊ አገራት በቂ ፋይናንስ ስለማይኖራቸው ለአየር ንብረት ተስማሚ የሆነ ኢኮኖሚ ለመገንባት እንደሚቸገሩ ጠቁመዋል።

ለዚህም በኢኮኖሚ የበለጸጉ አገራት የታዳጊ አገራትን አየር ንብረት ለውጥ የመቋቋሙን ሂደት በስራ ፈጠራና ቢዝነስ ሊደግፉት እንደሚገባም ገልጸዋል።

በደቡብ አፍሪካ ዓለም አቀፍ ጉዳዮች ኢንስቲትዩት የኃብት አስተዳደር ኃላፊ አሌክስ ቤንኬንስቲየን በአየር ንብረት ለውጥ የሚከሰተውን ችግር ለመቀነስ የፋይናንስ ተደራሽነትን ማፈላለግ ያስፈልጋል ብለዋል።

በቀጣይ በግብጽ የሚካሄደውን የዓለም አቀፍ የአየር ንብረት ለውጥ ድርድር ላይ የአፍሪካ አገራት በጋራ ድምጻቸውን ማስማት እንዳለባቸው ገልጸዋል።

በአየር ንብረት ለውጥ የሚደርሰውን ጉዳት ለመከላከል ፋይናንስ በማፈላለግ ላይ አጋር አካላትን ማስተባበር እንዳለባቸውም እንዲሁ፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም