ቀጥታ፡

የሥራና ክህሎት ሚኒስቴርና ሚድሮክ ኢንቨስትመንት ግሩፕ የሰለጠነ የሰው ኃይል ለማቅረብና ምርታማነትን ለማሳደግ በጋራ ለመስራት ተስማሙ

መስከረም 03/ 2015 (ኢዜአ) የሥራና ክህሎት ሚኒስቴርና ሚድሮክ ኢንቨስትመንት ግሩፕ የሰለጠነ የሰው ኃይል ለማቅረብ፣ ምርታማነትን ለማሳደግና የኢንዱስትሪ ደህንነትን ለማረጋገጥ በጋራ ለመስራት የሚያስችል ስምምነት ዛሬ በአዲስ አበባ ተፈራርመዋል።

ስምምነቱን የሥራና ክህሎት ሚኒስትሯ ሙፈሪያት ካሚል እና የሚድሮክ ኢንቨስትመንት ግሩፕ ዋና ስራ አስፈጻሚ ጀማል አህመድ ፈርመውታል፡፡

ሚኒስትሯ በዚሁ ወቅት እንደገለጹት፤ ስምምነቱ የኢንዱስትሪ ሰላምን በማረጋገጥ፣ የሙያ ደህንነት እና ጤንነት ባህልን በማሻሻል ረገድ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ይኖረዋል፡፡

ከሚድሮክ ኢንቨስትመንት ግሩፕ ጋር የግብርና፣ ቱሪዝም፣ ማዕድንና ሌሎች ዘርፎች ምርታማነትን ለማሳደግ እና የሙያ ደህንነትን ለመጠበቅ በጋራ እንደሚሰሩ ተናግረዋል።

ስምምነቱ የስራ እድል ከመፍጠር ባለፈ የስራ ባህልን በመቀየር እና የሰለጠነ እና ክህሎት ያለው የሰው ሀይል ለማፍራት የሚያግዝ ነው ብለዋል፡፡

የሚድሮክ ኢንቨስትመንት ግሩፕ ዋና ስራ አስፈጻሚ ጀማል አህመድ በበኩላቸው፤ ስምምነቱ መንግስት ኢንተርፕራይዞችን ለማስፋፋት፣ የስራ እድል ፈጠራ እና ክህሎትን ለማሻሻል፣ እንዲሁም የኢንዱስትሪ ሰላምን ለማረጋገጥ ለሚያደርገው እንቅሰቃሴ የላቀ ሚና እንደሚኖረው ገልጸዋል፡፡

ሚድሮክ ያለበትን የሰው ኃይልና የሥራ አመራር ክፍተቶች ለማስተካከል በጋራ መስራቱ መልካም አጋጣሚ ነው ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም