ኢትዮጵያ እንደ ደቡብ ኮሪያ ጠንካራ ኢኮኖሚ መገንባት የሚያስችል ትክክለኛ አቅጣጫ ላይ ትገኛለች- ዶክተር ቾ ሰንግ ሷ

18

መስከረም 3 /2015 (ኢዜአ) ኢትዮጵያ እንደ ደቡብ ኮሪያ ጠንካራ ኢኮኖሚ መገንባት የሚያስችል ትክክለኛ አቅጣጫ ላይ ትገኛለች ሲሉ የደቡብ ኮሪያ አለም አቀፍ የወጣቶች ህብረት ሊቀመንበር ዶክተር ቾ ሰንግ ሷ ገለጹ።

ከእስያ አገራት መካከል ከውስብስብ ችግሮች በመውጣት ፈጣንና አስደማሚ የኢኮኖሚ እድገት በማስመዝገብ ደቡብ ኮሪያ በግንባር ቀደምትነት ትጠቀሳለች።

የኢትዮጵያ ምጣኔ ሃብትም በተከታታይ ዓመታት ከፍተኛ እድገት እያሳየ ሲሆን በ2014 በጀት ዓመት እንኳን በብዙ ጫናዎች ውስጥም ሆኖ የ6 ነጥብ 6 በመቶ እድገት ተመዝግቦበታል።

የ2015 በጀት ለብዝሃ ዘርፍ የኢኮኖሚ እድገት ምንጮች እና የተረጋጋ ማክሮ ኢኮኖሚ ማስፈን ትኩረት የሰጠ ሆኖ ቀጥሏል።

በመሆኑም ኢትዮጵያ እንደ ደቡብ ኮሪያ ጠንካራ ኢኮኖሚ መገንባት የሚያስችል ትክክለኛ አቅጣጫ ላይ የምትገኝ መሆኑን የደቡብ ኮሪያ አለም አቀፍ የወጣቶች ህብረት ሊቀመንበር ዶክተር ቾ ሰንግ ሷ ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ አሁን ላይ የተለያዩ ችግሮች አጋጥመዋትም በእድገት መንገድ ላይ መሆኗን ጠቅሰው ሁሉንም በማለፍ ማደግ የሚያስችል አቅም አላት ብለዋል።

የኢትዮጵያ እምቅ የተፈጥሮ ሃብት፣ የልማትና የቱሪዝም ሃብት ያላት መሆኑና በግብርናው ዘርፍም የተሻለ ምርት እያገኘች መሆኑ በትክክለኛ የእድገት መስመር ላይ መሆኗን ያመላክታል ነው ያሉት።

የቀደምት የስልጣኔ ተምሳሌት የሆነችው ኢትዮጵያ አለም አቀፍ የዲፕሎማቶች ማእከል በመሆኗም ለብዙ ነገሮች መልካም አጋጣሚ የሚፈጥርላት መሆኑን ገልጸዋል።

በሁሉም መስኩ ኢትዮጵያ እንደ ደቡብ ኮሪያ ጠንካራ ኢኮኖሚ መገንባት የሚያስችል ትክክለኛ አቅጣጫ ላይ ትገኛለች ሲሉም ተናግረዋል።

ለአንድ አገር ሁለንተናዊ ዕድገት ብሄራዊ አንድነት፣ የትብብርና ጠንካራ የስራ ባህል መዳበር፣ የቴክኖሎጂና ዘመናዊ አሰራር፣ በውይይት መግባባት ላይ በመድረስ ልዩነትን ማጥበብ አስፈላጊ መሆኑን ይመክራሉ።

የደቡብ ኮሪያ አለም አቀፍ የወጣቶች ህብረት ሊቀመንበር ዶክተር ቾ ሰንግ ሷ በኢትዮጵያ በተለይም በከፍተኛ ትምህርትና መንግስታዊ ተቋማት ለስድስት አመታት የማይንድ ሴት ስልጠና ሰጥተዋል።

በቀጣይ ትምህርት ቤቶችና ወጣቶች ላይ በማተኮር ስልጠና የመስጠት እቅድ እንዳላቸውም ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም