የአፍሪካ የአረንጓዴ ለውጥ ጥምረት የምግብ ደህንነት ችግርን ለመፍታት እገዛ የሚያደርግ 550 ሚሊዮን ዶላር ድጋፍ አደረገ

119

መስከረም 03 ቀን 2015 (ኢዜአ) የአፍሪካ የአረንጓዴ ለውጥ ጥምረት (አግራ) በአፍሪካ የሚታየውን የምግብ ደህንነት ችግር ለመቅረፍ የሚሰራውን ስራ ለመደገፍ 550 ሚሊየን ዶላር ድጋፍ ማድረጉን አስታወቀ፡፡

የጥምረቱ የበላይ ጠባቂ እና የቀድሞ የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ሀይለማርያም ደሳለኝ ድጋፉ በመጪዎቹ አምስት ዓመታት ውስጥ አህጉሪቱ በምግብ ራሷን ለማስቻል የሚሰሩ ስራዎችን ለማበረታታት መሆኑን ገልጸዋል፡፡

የግብርና ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ በሚል በቀረጸው አዲስ ፖሊሲው መሰረት ከ15 የአፍሪካ ሀገራት 28 ሚሊዮን አርሶ አደሮችን የመረጠው ጥምረቱ፤ እ.አ.አ ከ2023 እስከ 2027 ድረስ የዘር አቅርቦት ስርዓትን ማሳደግ፣ የመንግስትን ተሳትፎ ማሳደግ፣ የግብርና ግብዓት አቅርቦት ሰንሰለትን ማጠናከርና የአየር ንብረት ለውጥን መቋቋም የሚያስችሉ ስራዎች ላይ ትኩረት ሰጥቶ እንደሚሰራ ተገልጿል።

እ.አ.አ ከ2015 እስከ 2020 ድረስ በነበሩት ዓመታት የግብርና ምርታማነት በየዓመቱ በአማካይ በ13 በመቶ ያድግ እንደነበር ያነሱት አቶ ሀይለማርያም፤ በአሁኑ ወቅት የምርጥ ዘር አቅርቦት ችግር እየሆነ መምጣቱን ገልጸዋል።

በአነስተኛ ማሳ የሚያርሱ አርሶ አደሮች በአየር ንብረት ለውጥ፣ በኮሮና ወረርሽኝ፣ በግብርና ግብዓቶች መወደድ እና በውጪ ጫናዎች ጭምር ለጉዳት እየተዳረጉ መሆኑን ጠቅሰዋል።

አርሶ አደሩ የሚያስፈልገውን ምርጥ ዘር በተመጣጣኝ ዋጋ እና ወቅቱ ሳያልፍ እንዲያገኝ ለማስቻል ጥረት እንደሚደረግ ገልጸዋል።

የጥምረቱ ፕሬዚደንት ዶክተር አግነስ ካሊባታ በበኩላቸው የአርሶ አደሩን ምርታማነት በማሳደግ ህይወቱ እንዲለወጥ ለማድረግ የግብርና ግብዓት በበቂ መጠን የሚያገኝበትን አማራጭ ማስፋት እንደሚገባ ጠቁመዋል።

አፍሪካ 50 ቢሊየን ዶላር ዋጋ ያለው የምግብ ሸቀጥ እንደምታስገባ ገልጸው፤ በራስ አቅም ማምረት ካልተቻለ ወጪው እ.አ.አ በ2030 ወደ 110 ቢሊዮን ሊያድግ እንደሚችል ገልጸዋል።

በመሆኑም የምግብ ደህንነትን ለማረጋገጥ በሚሰሩ ስራዎች ላይ መሰረታዊ ሽግግር ማድረግ እንደሚያስፈልግ አመላካች ነው ማለታቸውን ዘ ኢስት አፍሪካን በዘገባው አመልክቷል።

ኢትዮጵያን እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ፤

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም