ቀጥታ፡

በደቡብ ክልል አዲሱ ስርዓተ ትምህርት ከ1ኛ እስከ 8ኛ ክፍሎች ሙሉ በሙሉ ይተገበራል- ቢሮው

ጂንካ/ሆሳዕና መስከረም 3/2015 (ኢዜአ) በደቡብ ክልል በ2015 የትምህርት ዘመን አዲሱ ስርዓተ ትምህርት ከ1ኛ እስከ 8ኛ ክፍሎች ሙሉ በሙሉ ተግባራዊ እንደሚደረግ የክልሉ ትምህርት ቢሮ አስታወቀ ።

በደቡብ ኦሞና ሀዲያ ዞኖች የትምህርት ሳምንት መርሃ ግብር እየተካሄደ ነው።

በደቡብ ኦሞ ደረጃ ''ትምህርት ለሁሉም፤ሁሉም ለትምህርት” በሚል መሪ ሀሳብ የትምህርት ሳምንት መርሀ ግብር  በጂንካ ሚሊኒየም 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት እየተካሄደ ነው ።

በመርሃ ግብሩ ላይ የተገኙት የደቡብ ክልል ትምህርት ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ ተስፋዬ ደፋሩ እንደገለጹት  በክልሉ በ2015 የትምህርት ዘመን ከ1ኛ እስከ 8ኛ ክፍሎች አዲሱ ስርዓተ ትምህርት ሙሉ ለሙሉ  ተግባራዊ ይደረጋል ።

ለትግበራው በቂ ዝግጅት መደረጉን የተናገሩት ምክትል ኃላፊው ትግበራው ውጤታማ እንዲሆን ተማሪዎች፣ መምህራን፣ ርዕሳነ መምህራን እና ወላጆች የበኩላቸውን ሚና እንዲወጡ አሳስበዋል።

በስርዓተ ትምህርት ትግበራው መሰረት ዘንድሮ ለ6ኛ ክፍሎች ክልላዊ ፈተና እንደሚሰጥ ጠቅሰው  ተማሪዎች ለፈተናው በቂ ዝግጅት እንዲያደርጉ አሳስበዋል ።

የ8ኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተና ማለፊያ ነጥብም በአማካይ 50 እና ከዚያ በላይ ስለሚሆን ተማሪዎች ጠንክረው መማር እንዳለባቸው ተናግረዋል ።

በትምህርት ሳምንት ንቅናቄው በክልሉ የቅድመ መደበኛና መደበኛ ተማሪዎች ምዝገባ መቶ በመቶ ለማድረስና የመማር ማስተማሩን በተሟላ መልኩ ለመጀመር መታሰቡን ገልጸዋል።

የደቡብ ኦሞ ዞን አስተዳዳሪ አቶ ንጋቱ ዳንሳ በበኩላቸው በደቡብ ኦሞ ዞን የትምህርት ተደራሽነት 79 በመቶ መድረሱን ተናግረው ተደራሽነቱ ከሞላ ጎደል የተሻለ ቢሆንም ጥራትን ከማስጠበቅ አኳያ ውስንነቶች እንዳሉ ጠቁመዋል።

"የችግሩ መንስኤ ከሆኑት ምክንያቶች አንዱ ኩረጃ በመሆኑ ኩረጃን የሚፀየፍ ትውልድ በመገንባት በእውቀት የካበተ፣ በስነምግባር የታነፀ ብቁና አገር ተረካቢ ዜጋ መፍጠር አለብን" ብለዋል።

ለተግባራዊነቱ መምህራን እና ወላጆች የበኩላቸውን ሚና እንዲወጡ ጠይቀዋል።

የጂንካ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ ጉራልቅ ይዥማልቅ በበኩላቸው በዘንድሮው የትምህርት ዘመን እድሜያቸው ለትምህርት የደረሱ ህፃናት እንዲመዘገቡ የተለያዩ የንቅናቄ ስራዎች እየተሰሩ እንደሆነ ተናግረዋል።

የመማሪያ ቁሳቁስ ሟሟላት ለማይችሉ አቅመ ደካማ ቤተሰብ ያላቸው እና ወላጆቻቸውን ላጡ ተማሪዎች ከትምህርት ገበታው እንዳይነጠሉ ''አንድ ደርዘን ደብተር ለአንድ ተማሪ'' በሚል መሪ ሀሳብ የትምህርት ቁሳቁስ በማሰባሰብ ድጋፍ የማድረግ ስራ እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

በዘንድሮ ዓመት በከተማ አስተዳደሩ በሚገኙ ትምህርት ቤቶች የትምህርት ጥራትን በማስጠበቅ በአገር አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ የሆኑ ተማሪዎችን ለማፍራት በትኩረት እንደሚሰራ አመላክተዋል ።

በጂንካ ሚሊኒየም 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት በተካሄደው ሳምንታዊ የትምህርት ንቅናቄ መረሃ ግብር ላይ የክልሉ ትምህርት ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ ተስፋዬ ደፋሩ፣የክልሉ አርብቶ አደር ቢሮ ኃላፊ አቶ ሎሬ ካኩታ፣ የደቡብ ኦሞ ዞን አስተዳዳሪ አቶ ንጋቱ ዳንሳ ጨምሮ የትምህርት ማህበረሰቦችና የተማሪ ወላጆች ታድመዋል ።

በተመሳሳይ  በሀድያ ዞን "ትምህርት ለሁሉም ሁሉም ለትምህርት" በሚል መሪ ቃል የ2015 ዓ.ም የትምህርት ዘመን የመማር ማስተማር ስራ ማስጀመሪያ ስነ ስርአት በሆሳዕና ከተማ በሄጦ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት እየተካሄደ ነው።

በስነ ስርአቱ ላይ የብልጽግና ፓርቲ ማዕከላዊ ኮሚቴ አባልና የደቡብ ክልል ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ጥላሁን ከበደን ጨምሮ ሌሎች የክልሉና የዞኑ የመንግስት የስራ ሃላፊዎች፣ የሀድያ ዞን መምህራንና ተማሪዎች ተገኝተዋል።

ከስነ ስርአቱ ጎን ለጎን በህብረተሰብ ተሳትፎ እየተገነባ የሚገኘውን የበሊሎ ወንጭሶ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት እና በሶሮ ወረዳ የሚገኘውን የቆሻ ጤና ጣቢያ ግንባታ ጉብኝት እንደሚደረግ ተመላክቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም