በአዮዲን የበለጸገ ጨው ለተጠቃሚው ለማዳረስ እየተሰራ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በአዮዲን የበለጸገ ጨው ለተጠቃሚው ለማዳረስ እየተሰራ ነው
አዳማ መስከረም 9/2011 በአዮዲን እጥረት የሚከሰቱ በሽታዎችን ለመከላከል በአዮዲን የበለጸገ ጨው ለተጠቃሚው ለማዳረስ እየተሰራ መሆኑን የኢትዮጰያ የምግብ ፣መጠጥና ፋርማሲቲዩካል ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲትዩት ገለጸ። በአዮዲን የበለጸገ ጨው ለተጠቃሚው በስፋት ለማቅረብና ተደራሽነትን ለማሳደግ የሚያስችል የኢትዮጵያ ጨው አምራቾች እና አቀናባሪዎች ማህበር የጋራ ፎረም ተመስርቷል። የኢንስቲትዩቱ ዋና ዳይሬክተር አቶ ሰለሞን ታደለ ትናንት በቢሾፍቱ ከተማ በተካሄደው የፎረሙ ምስረታ ወቅት እንዳሉት በአዮዲንና ተያያዥ የምግብ ንጥረ ነገር እጥረት ለተለያዩ በሽታዎች ያጋልጣል፡፡ እነዚህ የአዕምሮ ውስንነት፣ጎይተርና የመቀንጨር በሽታዎችን ለመከላከል ሀገሪቱ በየዓመቱ ከፍተኛ ሀብት እያፈሰሰች ትገኛለች። በአዮዲንና ተያያዥ የምግብ ንጥረ ነገር እጥረት ምክንያት የሚከሰቱ በሽታዎችን ለመከላከልና ለማከም ሀገሪቱ ከ55 ቢሊዮን ብር በላይ እንደሚታወጣ አመልክተዋል። የጨው ሀብቱን በአዮዲን በማበልፀግ የሀገር ውስጥ ፍጆታን ከመሸፈን ባለፈ ለኢንዱስትሪ ግብዓት ለማቅረብ ምርቱ ዓለም አቀፍ ደረጃውንና ጥራትን በጠበቀ መልኩ እንዲመረት መንግስት እየሰራ መሆኑን አቶ ሰለሞን ተናግረዋል። በአዮዲን እጥረት የሚከሰቱ በሽታዎች ሀገሪቱ ብቁና በአእምሮ የበለጸገ የሰው ኃይል እንዳይኖራት የሚያደርግ መሆኑን የገለጹት ደግሞ በኢንስቲትዩቱ ተመራማሪ አቶ ፍቅሩ አበበ ናቸው። ህብረተሰቡ ስለአዮድን ጨው ጠቃሜታ ያለው ግንዛቤ አነሰተኛ በመሆኑ ይህን ችግር ለመፍታት ሀገር አቀፍ ንቅናቄ ለመፍጠር ጥረት እያደረጉ መሆኑን አመልክተዋል። በሀገሪቱ ገጠራማ አካባቢዎች አዮዲን ያለበት ጨው በስፋት እንደማይገኝ ጠቅሰው ህብረተሰቡ ጥሬ ጨውና በአዮዲን የበለጸገው ዋጋቸው በመለያየቱ ምክንያት ገዝቶ በመጠቀም ላይ ሰፊ ክፍተት መኖሩንም ተናግረዋል። በአሁኑ ወቅት ጨው የሚያመርቱ 10 ኢንዱስትሪዎች ይገኛሉ፡፡ እነዚህንና በቅርቡ በአዮዲን የበለጸገ ጨው የሚያመርቱ አራት ግዙፍ አምራቾችን ወደ ሥራ በማስገባት በጥራት ና በተመጣጣኝ ዋጋ ምርቱን ለህብረተሰቡ ተደራሽ ለማድረግ እየተሰራ መሆኑን አስረድተዋል። የኢትዮጵያ ጨው አምራቾች እና አቀናባሪዎች ማህበር የጋራ ፎረም መመስረት ያስፈለገው በገጠራማ የሀገሪቱ አካባቢዎች ያለውን የአዮዲን ጨው አቅርቦት እጥረት ችግር ለመፍታት ጭምር ነው ተብሏል። የጨው አምራቾች ተወካይና የመድረኩ ተሳታፊ አቶ ጌታቸው እሸቱ በበኩላቸው በአዮዲን የበለጸገ ጨው በማምረት በሀገሪቱ ለሚገኙ ትላልቅ ሆቴሎችና የኢትዮጵያ አየር መንገድ እያቀረቡ መሆኑን ተናግረዋል። በውስን አምራቾችና አቀናባሪዎች አሁን ያለውን የአዮዲን ጨው ፍላጎትና አቅርቦት ማጣጣም እንደማይቻል ጠቅሰው "ህብረተሰቡ እየቀረበለት ያለውን የአዮዲን ጨው ከግንዛቤ እጥረትና ከዋጋ አንፃር እየተጠቀመ አይደለም" ብለዋል። በህብረተሰቡ ውስጥ ያለውን የግንዛቤ ክፍተት በማስተካከል በአዮዲን የበለጸገ ጨው እንዲመገብ ሁሉንም ባለድርሻ አካላት ያሳተፈ ሥራ ተፈጻሚ ማድረግ እንደሚገባም አመልክተዋል። ጨው በየመንገዱ እየተፈጨ ህጋዊ እውቅና ባላቸው አምራቾችና አቀናባሪዎች ስም በየሱቆቹ እየተሸጠ መሆኑን ጠቅሰው ይህ ድርጊት የህዝብን ጤንነት አደጋ ላይ እንደሚጥል በመገንዘብ ትኩረት እንደሚያስፈልገውም ጠቁመዋል። በቢሾፍቱ ከተማ በተካሄደው የፎረሙ ምስረታ መድረክ የኢትዮጵያ ጨው አምራቾች እና አቀናባሪዎች ድርጅቶችና ባለሃብቶች፣ ተመራማሪዎችና የዘርፉ ሥራ ኃላፊዎች ተሳትፈዋል።