የአሸባሪው ሕወሓት ወረራ እስኪቀለበስ ድረስ የጀመርነውን የስንቅ ዝግጅት እናጠናክራለን---የደባርቅ ነዋሪዎች

27

ደባርቅ መስከረም 3/2015 (ኢዜአ) አሸባሪው ህወሓት የጀመረው ወረራ እስኪቀለበስ ድረስ ለወገን ጦሩ የሚያደርጉትን የስንቅ ዝግጅትና ድጋፍ አጠናክረው እንደሚቀጥሉ የደባርቅ ወረዳ ነዋሪዎች ተናገሩ።

ቡድኑ 3ኛ ዙር ወረራ ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ እስካሁን ድረስ የሰሜን ጎንደር ዞን ህዝብን በማስተባበር 1 ሺህ ኩንታል ደረቅ ስንቅ በማቅረብ ደጀንነቱን እያሳየ ይገኛል።

የአሸባሪው ወረራ እስኪቀለበስ ድረስ ደጀነነታቸውን አጠናክረው እንደሚቀጥሉ በስንቅ ዝግጅቱ እየተሳተፉ ያሉ ነዋሪዎች ተናግረዋል። 

የደባርቅ ወረዳ ነዋሪ ወይዘሮ ፈንታ ተክሉ ለኢዜአ እንዳሉት ቡድኑ የአማራን ሕዝብ ለማዋረድና ኢትዮጵያን ለመበተን ወረራ ፈጽሟል። 

እሳቸው ከሌሎች የአከባቢው ነዋሪዎች ጋር በመሆን በግንባር ለተሰለፈው የወገን ጦር ስንቅ እያዘጋጁ መሆናቸውን ተናግረዋል።  

“ቡድን በፈጸመው ወረራ ሕጻናትና እናቶችን ጭምር እየገደሉ ነው” ያሉት ወይዘሮ ፈንታ፣ ልጆቻቸውጭምር የሽበብር ቡደኑን በግንባር እየተፋለሙ መሆኑን ገልጸዋል። 

ሌላዋ የቀበሌው ነዋሪ ወይዘሮ ሙሃባ አዘዘው በበኩላቸው ቡድኑን በግንባር እየተፋለመ ለሚገኘው የሀገር መከላከያ ሠራዊት እና ሌሎች የጸጥታ ሀይሎች ስንቅ እያዘጋጁ መሆኑን ጠቅሰዋል።

"ሰላም ከሌለ ሀገር የለም" ያሉት ወይዘሮ ሙሃባ፣ "ኢትዮጵያ ሰላም እስክታገኝ ድረስ ሁላችንም ከስንቅ ዝግጅት ባለፈ አሸባሪውን ቡድን በግንባር ለመፋለም መዘጋጀት ይኖርብናል” ብለዋል። 

"አካባቢያችንን ከሽብር ቡድኑ ሰርጎ ገቦች ነቅተን በመጠበቅና በስንቅ ዝግጅት የኋላ ደጀንነት ተግባራችንን እየተወጣን ነው" ያሉት ደግሞ በስንቅ ዝግጅት ላይ እየተሳተፉ ያሉት ወይዘሮ አደባባይ ጥላሁን ናቸው።

ቡድኑን ለመደምሰስ መዋጋት የሚችለው በግንባር፣ ለመዋጋት አቅም የሌለው ደግሞ ሌሎች ሥራዎችን በመስራት እየተሳተፈ መሆኑንም ተናገርዋል።

የደባርቅ ወረዳ ብልፅግና ፓርቲ አደረጃጀት ዘርፍ ኃላፊ ወይዘሮ ትግስት አቡሃይ በበኩላቸው፣ የአካባቢው ነዋሪዎች ለመከላከያ ሠራዊትና ሌሎች የጸጥታ ሀይሎች ስንቅ እያዘጋጁ መሆኑን አረጋግጠዋል።

የወረዳው አርሶ አደር "ቅድሚያ ጠላትን በግንባር እየመከተ ለሚገኘው ሠራዊት” በሚል የምግብ እህል መሰብሰቡን ገልጸው።

"ወረራውን ለመቀልበስ ለወገን ጦር የስንቅ ዝግጅት እየተደረገ ነው” ያሉት ደግሞ የሰሜን ጎንደር ዞን ሴቶች፣ ሕጻናትና ማህበራዊ ጉዳይ መምሪያ ኃላፊና የዞኑ የስንቅ ዝግጅት ንዑስ ኮሚቴ አስተባባሪ ወይዘሮ ባንችአምላክ መልካሙ ናቸው። 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም