አሸባሪው ህወሓት ለስልጣን ጥማቱ ሲል በሐሰት ፕሮፓጋንዳ ጠላት ከቦሃል በማለት የትግራይን ወጣት በጦርነት እየማገደ ነው - እጃቸውን የሰጡ የሽብር ቡድኑ ታጣቂዎች

14

መስከረም 03 ቀን 2015 (ኢዜአ) አሸባሪው ህወሓት ለስልጣን ጥማቱ ሲል በሐሰት ፕሮፓጋንዳ በጠላት ተከበሃል በማለት የትግራይን ወጣት በጦርነት እየማገደ ነው ሲሉ እጃቸውን የሰጡ የሽብር ቡድኑ ታጣቂዎች ገለፁ።

በምዕራብ ግንባር የተማረከው አስመሮም ወልደሚካኤል አሸባሪው ቡድን ‘የትግራይ ህዝብ በጠላት ተከበሃል ነፃ የምትወጣው ታግለህ ማሽነፍ ስትችል ነው’ በሚል የተሳሳተ መንገድ ህፃናትንና አረጋውያንን በግዳጅ ወደ ጦር ግንባር በማስገባት እያስጨረሰው ይገኛል ሲል ለኢዜአ ገልጿል።

ለቡድኑ ስልጣን ሲል ወደ ጦርነት እሳት ውስጥ ተገዶ የገባው ወጣት ለአገር መከላከያ ሰራዊት እጁን በመስጠት ህይወቱን ሊያተርፍ ይገባል ሲል መክሯል።

ሌላዋ የ17 ዓመት ታዳጊ መሰረት ተክላይ ጥቂት የስልጣን ጥማት ባላቸው አሸባሪዎች ምክንያት የትግራይ ህዝብ በጦርነት እያለቀ ነው ብላለች።

May be an image of 5 people, people sitting, people standing and outdoors

ወጣቱን በግዳጅ ወደ ጦርነት በማስገባት እልቂት እየተፈፀመበት እንደሆነ ገልፃ፤ እርሷም በግዳጅ እንድትገባ ቢደረግም ከነሙሉ ትጥቋ ለመከላከያ ሰራዊት እጇን መስጠቷን ተናግራለች።

አሁን እኔ እድለኛ ነኝ ያለችው እጇን የሰጠችው የሽብር ቡድኑ ታጣቂ በርካታ ህፃናትና ወጣቶች በጦርነቱ እንዳለቁ ገልፃለች።

የመከላከያ ሰራዊትና ሌሎች የፀጥታ ሃይሎች እርምጃ ይውስዱባችኋል እጃችሁን እንዳትሰጡ በማለት ያስፈራሩ እንደነበር አውስታ፤ ነገር ግን በተግባር ያልጠበቁት እንክብካቤ ማግኘቷን አስታውቃለች።

የህወሃት የሽብር ቡድን ከትምህርት ገበታ በማስወጣት በግዳጅ ወደ ጦርነት በማስገባት የበርካታ ወጣቶችን ተስፋ እያጨለመ ነው ያለችው ደግሞ ሌላዋ የ20 ዓመት ወጣት አፀደ ወልደሚካኤል ናት።

ትምህርቷን አቋርጣ ወደ ጦርነት መግባቷን ጠቅሳ፤ በጦርነቱ ወጣቱ እያለቀ ነው ብላለች።

እጇን ለመከላከያ በመስጠት ህይወቷን በማትረፏ እድለኛነቷን ገልፃ፣ በግንባር የሚገኘው ወጣትም በሰላም እጁን በመስጠት ህይወቱን እንዲያተርፍ ጥሪ አስተላልፋለች።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም