ኢንስትራክተር አብርሃም መብራቱ በፊፋ የቴክኒክ ባለሙያ ሆነው ተሾሙ - ኢዜአ አማርኛ
ኢንስትራክተር አብርሃም መብራቱ በፊፋ የቴክኒክ ባለሙያ ሆነው ተሾሙ
መስከረም 3 ቀን 2015(ኢዜአ) የካፍ ኤሊት ኢንስራትክተርና የባህር ዳር ከተማ እግር ኳስ ክለብ አሰልጣኝ አብርሃም መብራቱ በዓለም አቀፉ የእግር ኳስ ማኅበር(ፊፋ) የቴክኒክ ባለሙያ ሆነው ተሾሙ።
አሰልጣኝ አብርሃም በዚህ ዘርፍ የተሾሙ የመጀመሪያው ኢትዮጵያዊ ኢንስትራክተር መሆናቸውን የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን አስታውቋል።
ኢንስትራክተር አብርሃም ፊፋ ለቴክኒክ የላቀ ባለሙያነት ያቀረባቸውን መመዘኛዎች በማለፍ እንደ ሁኔታው በሚታደስ የሁለት ዓመት ኮንትራት በቦታው ላይ መሾማቸው ተመልክቷል።
በአፍሪካ በኤሊት ኢንስትራክተርነት፣ በአፍሪካ ዋንጫና መሰል ትልልቅ ውድድሮች በቴክኒክ ጥናት ቡድን አባልነትና አሰልጣኝነት እንዲሁም በእስያና በየመን እግር ኳስ ላይ ያላቸው የስራ ልምድ ለቦታው ተመራጭ እንዳደረጋቸው ተገልጿል።
በፊፋ የቴክኒክ ኤክስፐርትነት ከሚሰጣቸው ተግባራት መካከል በኤሊት የእግር ኳስ አሰልጣኝነት ፣ በወጣቶች እግር ኳስ ፣ በግራስ ሩት ፣ ለኢንስትራክተሮች እና ከእግር ኳስ ጋር ተዛማጅነት ባላቸው ጉዳዮች ዙርያ ትምህርቶች/ ጽሑፎች ማዘጋጀት ይጠቀሳሉ።
ለአባል ሀገራት እና አህጉራዊ ኮንፌዴሬሽኖች በእግር ኳስ ልማት ዙርያ የቴክኒክ ማማከር ፣ የአባል ሀገራት የእግር ኳስ ልማት ፕሮግራሞች እና ተግባራትን መከታተል፣ አዲሱ የፊፋ ቴክኒክ ልማት ፕሮግራም ዝግጅትና አስፈላጊ ሰነዶች ዝግጅት ላይ መሳተፍ ከሚያከናውኗቸው ስራዎች መካከል እንደሚገኙበት ፌዴሬሽኑ አመልክቷል።
ኢንስትራክተር አብርሃም መብራቱ በፊፋ በተሰጣቸው የስራ ኃላፊነት ውጤታማ እንዲሆኑ ምኞቱን ገልጿል።