ለጀግናው የመከላከያ ሰራዊት ስንቅ ከማቀበል ጀምሮ የሚጠበቅብንን እንወጣለን- የሆስዕና ከተማ ሴቶች - ኢዜአ አማርኛ
ለጀግናው የመከላከያ ሰራዊት ስንቅ ከማቀበል ጀምሮ የሚጠበቅብንን እንወጣለን- የሆስዕና ከተማ ሴቶች
ሆስዕና ፤ መስከረም 2015(ኢዜአ) ለጀግናው የሀገር መከላከያ ሰራዊት ስንቅ አዘጋጅተው ከማቀበል ጀምሮ የሚጠበቅባቸውን የዜግነት ግዴታቸውን እንደሚወጡ በሀድያ ዞን ሆስዕና ከተማ ሴቶች ገለጹ።
ሁሉም የሚያምረው ከሀገር ሰላም መጠበቅ ጋር በመሆኑ ይህንን እየተፈታተነ ያለውን አሸባሪ ቡድን እየተፋለመ ለሚገኘው ለመከላከያ ሰራዊት የደጀንነት ድጋፋቸውን እንደሚያጠናክሩ አስታውቀዋል።
በሆሳዕና ከተማ የሊች አምባ ቀበሌ ነዋሪ ወይዘሮ ብርቱካን ጌሪቦ፤ አሸባሪው የህወሓት ቡድን ሀገሪቱን በበላይነት ከተቆጣጠረበት ጊዜ ጀምሮ በተከተለው ከአብሮነት ይልቅ የመከፋፈል ሀሳብ ሀገርን ለመበታተን ሲሞክር እንደቆየ ተናግረዋል።
ቡድኑ ሀገርን ለጠላት አሳልፎ ለመስጠት ሲያሴር መቆየቱንና በዚህ እኩይ ድርጊቱ የተማረረው መላው የሀገሪቱ ዜጋ ከስልጣኑ እንዲወርድ ማድረጉን አስታውሰዋል።
የሀገሪቱን ሰላምና ህልውና አስጠብቆ ለማስቀጠል የቡድን ሴራና እኩይ ዓላማ በማምከን ሉአላዊነቷን ለማስከበር እየተዋደው ለሚገኘው ለጀግናው የሀገር መከላከያ ሰራዊት ስንቅ ከማቀበል ጀምሮ የሚጠበቅባቸውን የዜግነት ግዴታቸውን እንደሚወጡ ገልጸዋል።
የሄጦ ቀበሌ ነዋሪ ወይዘሮ ደሳለች ማርቆስ በበኩላቸው፤ አሸባሪው የህወሐት ቡድን ሀገር የማፍረስ ሴራውን ተግባራዊ ለማድረግ ሲደራጅ ቢቆይም በጀግኖች የኢትዮጵያ ልጆች ሴራውን መምከን መቻሉን ተናግረዋል።
ቡድኑ መንግስት ያቀረበለትን የሰላም አማራጭ ወደ ጎን በመተው ዳግም ጦርነት ማወጁን ጠቁመዋል።
እኛ እናቶች ከሀገራችን የምናስቀድመዉ አንዳች ነገር ባለመኖሩ ልጆቻችንን መርቀን ከመሸኘት ባለፈ ግንባር ድረስ በመዝመት ለጀግናው የመከላከያ ሰራዊት ስንቅ በማቀበልና በሌላም ድጋፋችንን ለማጠናከር ዝግጁ ነን ብለዋል።
ሀገራችን ህልውናዋ ተጠብቆ የኖረው ያለ ተጋድሎና መስዋዕትነት አይደለም ያሉት ደግሞ የቦብቾ ቀበሌ ነዋሪ ወይዘሮ እንዳሻሽ ፀጋዬ ናቸው።
ለዚህ ደግሞ ደማቸውን አፍስሰውና አጥንታቸውን ከስክሰው ሀገር ያስቀደሙ የአባቶች ወኔ በመላበስ ዛሬም በክንደ ብርቱ ልጆቿ ክብሯ ተጠብቆ እንደሚቀጥል በተግባር መረጋገጡን ገልጸዋል።
ሀገሪቱን በመበዝበዝ ለእድገቷ ማነቆ በመሆን ወደ ኋላ ሲጎትት የኖረው ቡድኑ ዛሬም ያን ዕድል ለማግኘት የሚያደርገውን ሙከራ ለማክሸፍ እየተደረገ ባለው ተጋድሎ የድርሻቸውን እንደሚወጡ ተናግረዋል።
ቡድኑ ለእኩይ ድርጊት የትግራይን ህዝብ መሸሸጊያ በማድረግ አሁንም ህጻናት ከፊት አሰልፎ ለጦርነት መማገዱ የጭካኔው ጥግ እንደሚያሳይ ጠቅሰው፤ የትግራይ ሴቶች ከእኛ ጎን በመሆን ቡድኑን ሊታገሉ ይገባል ሲሉ መልዕክት አስተላለፈዋል።
አሸባሪው የህወሃትን ቡድን ለመደምሰስ በጀግንነት እየተፋለመ ላለው የሀገር መከላከያ ሰራዊት ስንቅ ከማቀበል ጀምሮ የሚጠበቅባቸውን የዜግነት ግዴታቸውን ለመወጣት ዝግጁ መሆናቸውን ነው አስተያየት ሰጪዎቹ የገለጹት።