ቀጥታ፡

በማህበረሰብ አቀፍ ፖሊስ ተደራጅተን የአካባቢያችንን ሰላም እየጠበቅን ነው- የሐረሪ ክልል ነዋሪዎች

ሐረር፤ መስከረም 2/2015(ኢዜአ) በማህበረሰብ አቀፍ ፖሊስ አገልግሎት ተደራጅተው ወንጀልን በመከላከል የአካባቢያቸውን ሰላም እየጠበቁ መሆናቸውን የሐረሪ ክልል ነዋሪዎች አስታወቁ ።

በክልሉ  የማህበረሰብ አቀፍ ፖሊስ አገልግሎት በምሽት ጭምር ከተጀመረ ወዲህ  ይፈፀሙ  የነበሩ ወንጀሎች  እየቀነሱ መምጣታቸውን የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽነር ገልጸዋል፡፡

ከነዋሪዎቹ መካከል ወጣት ክፍሌ ሙሉጌታ ፤  ሰላምን በፀጥታ ሃይሎች ብቻ ማስጠበቅ ስለማይቻል  ተደራጅተው የአካባቢያቸውን ሰላም በንቃት እየጠበቁ እንደሚገኙ ለኢዜአ ተናግሯል  ፡፡

ሰላም ከሌለ መኖር አይቻልም ያለው ወጣት ክፍሌ፤ በሰላም ጉዳይ ትልቅ ትኩረት በመስጠት ከፀጥታ ሃይሉ ጋር በመሆኑ አካባቢያቸውን በመጠበቅ ላይ መሆናቸውን ገልጿል፡፡

አቶ ደመቀ እምጅና በበኩላቸው፤  በማህበረሰብ አቀፍ የፖሊስ አገልግሎት በተከናወነው ጠንካራ ስራ በመንግስት ሲፈለጉ የነበሩ የአሸባሪው  የሸኔ  ቡድን አባላትን ጭምር በቁጥጥር ስር ማዋል መቻሉን ጠቁመዋል፡፡

በአካባቢያቸው  ፀጉረ ልውጦች እየበዙ ነው ያሉት አቶ ደመቀ፤  ሁሉም  ከፖሊስ ጋር በመተባበር አካባቢውን ነቅቶ እንዲጠብቅ መልዕክት  አስተላልፈዋል ፡፡

በራሳቸው ተነሳሽነት የአካባቢያቸውን ሰላም ለመጠበቅ ዘብ መቆማቸውን በመግለፅ ህብረተሰቡ ከፖሊስ ጋር ከተባበር በሰላም ረገድ የሚፈለገውን ለውጥ ማምጣት እንደሚቻል የገለጹት ደግሞ  ወይዘሮ አሰለፍ ሽፈራው ናቸው።

የሐረሪ ክልል ፖሊስ  ኮሚሽነር ነስሪ ዘካሪያ ፤ ወንጀልን ለመከላከል ማህበረሰቡን በብሎክ በማደራጀት እየተሰራ እንደሚገኝ ተናግረዋል።

 በክልሉ ለሰፈነው ሰላም የማህበረሰብ አቀፍ ፖሊስ አገልግሎት ትልቁን ድርሻ እንደሚወስድ አመልክተው፤ ማህበረሰቡ የሰላም ባለቤት እኔ ነኝ በሚል መንፈስ ሁሉም የአካባቢውን ሰላም እየጠበቀ ያለበት ሁኔታ መኖሩን ጠቁመዋል።

የማህበረሰብ አቀፍ ፖሊስ ሲደራጅ ቅድመ ወንጀልን መከላከል ስራን መሰረት አድርጎ ነው የሚሰራው ያሉ ኮሚሽነሩ፤ ማህበረሰቡ በዚህ ስራ ላይ ከተሰማራ ወዲህ ይፈፀሙ የነበሩ የስርቆት እና ሌሎች ወንጀሎችም እየቀነሱ መምጣታቸውን ገልጸዋል፡፡

ፀረ ሰላም ቡድኖች ሊያደርሱት የሚችሉትን ጥፋት ቀድሞ ከመከላከል ረገድ አበረታች ውጤት የተመዘገበበት መሆኑንና ወንጀልን የመከላከሉ ስራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ተናግረዋል፡፡

የማህበረሰብ አቀፍ ፖሊስ አገልግሎት በተለይ በዓላት በሚኖሩበት ወቅት ከፀጥታ ሀይሎች ጋር በመሆን ያለምንም የፀጥታ ችግር እንዲከበሩ ሚናቸው የጎላ መሆኑን የገለጹት ደግሞ የሐረሪ ክልል የማህበረሰብ አቀፍ ፖሊስ አገልግሎት  ዳይሬክተር ምክትል ኮማንደር ታጁ ኡመር ናቸው  ፡፡

በክልሉ የማህበረሰብ አቀፍ ፖሊስ  አገልግሎት  የራሱ ንዑስ ጣቢያ ኖሮት 24 ሺህ የሚደርሱ  የየአካባቢውን ማህበረሰብ አባላትን በማቀፍና የተለያዩ አደረጃጀቶችን በመፍጠር  የጸጥታ ስራውን  በየምሽቱ በማከናወን ላይ እንደሚገኝ አስረድተዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም