ቀጥታ፡

ለኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላምና የስኬት ጉዞ መቃናት ሁሉም በጋራ እንዲቆም የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ጥሪ አቀረበ

መስከረም 2/2015 /ኢዜአ/ በአዲሱ ዓመት ለኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላምና የስኬት ጉዞ መቃናት ሁሉም በጋራ እንዲቆም የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ጥሪ አቀረበ።

የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ሰብሳቢ ፕሮፌሰር መስፍን አርዓያ የተጠናቀቀውን ዓመትና 2015 አዲስ ዓመትን በሚመለከት የተለያዩ ሃሳቦችን አንስተዋል።

ኮሚሽነሩ ከኢዜአ ጋር በነበራቸው ቆይታ እንዳሉት የሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት፣ በተወሰኑ አካባቢዎች ያሉ ግጭቶች፣ የዜጎች መፈናቀልና ሞት እንዲሁም ዓለም አቀፋዊ ጫናዎች በ2014 ዓ.ም በእጅጉ ፈታኝ ነበሩ ሲሉ አስታውሰዋል።

በአንጻሩ የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ሶስተኛ ዙር ሙሌት መጠናቀቅ እና ሁለተኛው ተርባይን ማመንጨቱ እንዲሁም በመስኖ ልማት የስንዴ ምርት የተመዘገበው የላቀ ውጤት ተስፋ ሰጪ መሆኑን ጠቅሰዋል።

በመሆኑም የ2015 ዓ.ም ለኢትዮጵያውያን ሰላም የሰፈነበት እና የበለጠ የልማት ውጤቶች የምናሳካበት ዓመት እንዲሆን ሁላችንም የሚጠበቅብንን ማድረግ አለብን ብለዋል።

በጦርነት የተጎዱ ወገኖቻችን ክሰን ይቅርታ በመጠያየቅና መልሰን በማቋቋም የኢትዮጵያን ጅምር የሰላምና የልማት ተስፋዎች እውን ማድረግ አለብን ነው ያሉት።

ኢትዮጵያውያን ለሀገራዊ ምክክሩ ቀና ትብብርና ተሳትፎ በማድረግ ችግሮችን በጠረጴዛ ዙሪያ ተቀራርበን አንምከር በማለት ጥሪ አቅርበዋል።

የኢትዮጵያ ሁለንተናዊ የልማት እቅዶች አንዲሳኩ ፖለቲከኞች፣ ልሂቃን እንዲሁም አጠቃላይ ማህበረሰቡ ቀናዒ ትብብርና ተሳትፎ እንዲያደርጉ ጠይቀዋል።

በተለይ ወጣቶች ከስሜታዊነት ይልቅ በንግግርና ምክክር በማመን ለአገር ሰላምና ልማት ዋነኛ ባለቤትና አጋዥ እንዲሆኑ አስገንዝበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም