ቀጥታ፡

ዩ ኤስ ኤይድ ለኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን ስምንት ተሽከርካሪዎችን አበረከተ

መስከረም 2/2015 /ኢዜአ/ የአሜሪካ ተራድኦ ድርጅት /ዩ ኤስ ኤይድ/ ለኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን ስምንት ተሽከርካሪዎችን ድጋፍ አደረገ።

በኢትዮጵያ የአሜሪካ አምባሳደር ትሬሲ አን የተሽከርካሪዎቹን ቁልፍ ለኮሚሽኑ ምክትል ዋና ኮሚሽነር ራኬብ መለሰ አስረክበዋል።         

አምባሳደር ትሬሲ፤ የሰብአዊ መብት ላይ የሚሰራው ስራ የኢትዮጵያን መጻኢ እድል የተሻለ ለማድረግ ወሳኝ መሆኑን በዚሁ ጊዜ ተናግረዋል።     

የአሜሪካ መንግስት በሰብአዊ መብቶች ዙሪያ ኮሚሽኑ የሚያከናውናቸውን ተግባራት መደገፉን አጠናክሮ እንደሚቀጥልም አረጋግጠዋል።    

"ለድጋፍ እዚህ በመገኘቴ በጣም ደስተኛ ነኝ፤ ድጋፉ ኮሚሽኑ በቀጣይ የሚሰራቸውን ስራዎች ለማስፋት እድል ይፈጥራል የሚል እምነት አለኝ"  ሲሉም ተናግረዋል።  

በሰብአዊ መብት በኩል ተጠያቂነትን ማረጋገጥ ለአንድ አገር ዘላቂ ሰላም ቁልፍ ጉዳይ መሆኑንም አምባሳደሯ ተናግረዋል።           

የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን ተስፋ ሰጪ ጅምሮችን እያየንበት ነው ያሉት አምባሳደሯ ጅምሩ የበለጠ እንዲጠናከር አስፈላጊው ሁሉ ድጋፍ እናደርጋለን ብለዋል።   

የኮሚሽኑ ምክትል ዋና ኮሚሽነር ራኬብ መለሰ፤ በመላ አገሪቷ የተለያዩ ሰብአዊ መብቶች ክትትልና ምርመራ በማድረግ ኮሚሽኑ በትኩረት እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል።    

ሰብአዊ መብቶች ዙሪያም በተለያዩ የአገሪቷ ክፍል የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራዎችን እያካሄደ መሆኑን ጠቅሰው የዩ ኤስ ኤይድ የተሽከርካሪ ድጋፍ ለዚህ ተግባር ትልቅ እገዛ አለው ብለዋል።

ለተደረገልን ድጋፍ በኢትዮጵያ የአሜሪካን ኢምባሲ እንዲሁም ዩ ኤስ ኤይድን ማመስገን ይገባናል ብለዋል።   

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም