በቡና ምርት ልማትና የንግድ እንቅስቃሴ የላቀ ሚና ለነበራቸው የዘርፉ ተዋናዮች እውቅና እና ሽልማት ሊሰጥ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በቡና ምርት ልማትና የንግድ እንቅስቃሴ የላቀ ሚና ለነበራቸው የዘርፉ ተዋናዮች እውቅና እና ሽልማት ሊሰጥ ነው
መስከረም 2/2015 /ኢዜአ/በቡና ምርት ልማትና የንግድ እንቅስቃሴ የላቀ ሚና ለነበራቸው የዘርፉ ተዋናዮች እውቅና እና ሽልማት ሊሰጥ መሆኑን የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለስልጣን ገለጸ።
የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለስልጣን ምክትል ዋና ዳይሬክተር ሻፊ ኡመር፤ከመስከረም 4 እና 5 ቀን 2015 ዓ.ም የሚከበረውን የኢትዮጵያ ቡና ቀን በማስመልከት መግለጫ ሰጥተዋል።
የኢትዮጵያ የቡና ቀን "ቡናችን ለአብሮነታችንና ለብልፅግናችን” በሚል መሪ ሃሳብ ለሁለት ቀናት በተለያዩ መርሃ ግብሮች የሚከበር መሆኑን ተናግረዋል።
በመርሃ ግብሩ ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ሃላፊዎችና ባለሙያዎችን ጨምሮ ከ1 ሺህ በላይ የቡና፣ ሻይ እና ቅመማ ቅመም ዘርፍ የተሰማሩ አርሶ አደሮች፣ የቡና አቅራቢዎች፣ ላኪዎች እና ሌሎች የዘርፉ ተዋናዮች የሚገኙ መሆኑን ጠቁመዋል።
የቡና ምርትን ለማሳደግ በሚያስችሉ ርእሰ ጉዳዮች ላይ የሚያተኩሩ የውይይት መድረኮች እንደሚኖሩም ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ ገልጸዋል።
እለቱ ሲከበር ከ200 በላይ ለሚሆኑ በቡና፣ ሻይና ቅመማ ቅመም ዘርፍ ተሰማርተው የላቀ ውጤት ላሳዩ የዘርፉ ተዋናዮች እውቅና እና ሽልማት የሚሰጥ ይሆናል ብለዋል፡፡
ከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ እንዲገኝ የላቀ ሚና ለነበራቸው አርሶ አደሮች፣ ቡና ላኪዎች፣ መንግስታዊና ያልሆኑ ድርጅቶች እውቅና እና ሽልማት ከሚሰጣቸው መካከል መሆናቸውንም ተናግረዋል።
በ2014 በጀት ዓመት ከውጪ ንግድ ከተገኘው 4 ነጥብ 12 ቢሊየን ዶላር 1 ነጥብ 4 ቢሊየን ዶላሩ ከቡና የተገኘ መሆኑ ይታወቃል።
በ2015 በጀት ዓመት 360 ሺህ ቶን ቡና ለውጪ ገበያ በማቅረብ 2 ቢሊየን ዶላር ለማግኘት የታቀደ ሲሆን ከሌሎች ለውጭ ገበያ የሚቀርቡ ሌሎች ምርቶችን ጨምሮ በተያዘው በጀት ዓመት ከወጪ ንግድ 5 ነጥብ 4 ቢሊየን ዶላር ለማግኘት ታቅዷል።