በብዙ ፈተና ውስጥ የደመቀ ሳቅ!! - ኢዜአ አማርኛ
በብዙ ፈተና ውስጥ የደመቀ ሳቅ!!
በቀደሰ ተክሌ - ሚዛን አማን (ኢዜአ) የስኬትና ብልጽግና መንገድ ብዙ እሾህና አሜኬላ ያለበት፣ መውጣት መውረድ የሚበዛበት፣ ቀቢጸ ተስፋ የሚፈጠርበትና ዳግም የሚታደስበት የድካም ጉዞ ነው።
ኢትዮጵያ እየገጠማት ያለው ችግርና ፈተና ደግሞ የዚህ አምሳል ነው። ፈተናና ችግሮቿ የውድቀት ሳይሆኑ የስኬትና ዕድገት ማማ መቆናጠጫ መሰላሎች ናቸው። ለዚህም መከራና ስቃይ የበዛ በሚመስለን የኢትዮጵያ ፈተና ውስጥ በርካታ ሳቆችን ማየታችን ማረጋገጫ ነው።
የእናት ጡት ነካሽ ከብብቷ ስር ሆኖ ጦር መዞ የወጋት ሀገር ኢትዮጵያ የውጭ ጠላቶቿ ማበር ያጋጋለውን እሳት ተጋፍጦ ለመመከት መሪዋ እንኳ በዘመተበት አስቸጋሪ በሚባል ሁኔታ ውስጥ ሆና ስትስቅ ተመልክተናል። ኢትዮጵያ ፈርሳለች፣ ኢትዮጵያ ሰላም አይደለችም የሚል ፕሮፓጋንዳ በነዙበት በዛ ወቅት ኢትዮጵያ ሰላም ነች ሰላም ብቻ ሳትሆን ስትስቅ ነበር።
አሸንፌያለሁ ያለው የወሬ ባላበት አሸባሪው ህወሓት ከታሪካዊ ጠላቶች ጋር በመተባበር የፈጠረውን የጥፋት ሰንሰለት ኢትዮጵያ በጀግኖች ለጆቿ ብርቱ ትግልና ክንድ በጣጥሳ እየተሻገረች ነው። በዚሁ ሂደት ለጠላቶች ውርደት አከናንባ በምትፈጽማቸው መደበኛ ክዋኔና ተግባራት ደማቅ ሳቅ ታስተጋባ ነበር።
ከእነዚህ የሳቅ ምንጮቿ መካከል ዋና ዋናዎቹን እነሆ ለአብነት ማንሳቱ ጉዳዩን "ነገር በምሳሌ ጠጅ በብርሌ እንደሚባለው" ያደርገዋልና የተወሰኑትን ልጥቀስ። በህልውና ዘመቻ ላይ ሆነን የተቀበልነው አዲሱ ዓመት 2014 ከወትሮ የተለየ መደብዘዝ አልታየበትም።
ከሃይማኖታዊ እና ባህላዊ የአደባባይ በዓላት መካከል የመስቀል እና የኢሬቻ በዓለት በሰላም ተከብረው የጠላትን እጅ ከአፉ አስጭኗል። ጠላት ግን ደስታውን በወሬ ብቻ ቀጭቶ በዱር በገደል ሆኖ ኢትዮጵያ በአደባባይ ሆና ከበሮ እየደለቀች፣ ጥሩንባ እና መለከት እየነፋች ፈጣሪዋን ስታመሰግን ጋላቢዎቹ አንዳንድ ምዕራባውያን ንዴት በቀላቀለ ግርምት ተመልክተዋል።
መቼስ "ድሮም ኢትዮጵያን እናሸንፋለን ብሎ ማሰብ..." ሳይሉም አይቀርም! አንዳንዶች ኢትዮጵያ ጠንካራ መንግስት እንዲኖራት ከቶውንም አይፈልጉም። እንደ አሸባሪው ሕወሓት ተላላኪ የሆነና የእነሱን ፈላጎት የሚያስፈጽም መንግስት በኢትዮጵያ ምድር እንዲፈጠር ነው የሚሹት።
ይህንንም ለማሳካት ስድስተኛ ሀገራዊ ምርጫን በማጨናገፍ ትርምስ ለመፍጠር ምቹ ሁኔታዎችን ሲፈልጉና ብዙ ጉድጓዶችን ሲምሱ ታይተዋል።
በተለይ ኢትዮጵያ የገጠማት የውስጥ ጠላት ህወሓት ለጉዳያቸው አስፈጻሚ እንደሚሆን ተስፋ ሲያደርጉ አከርካሪው ተመትቶ ወደ መጣበት ሲመለስ ተስፋቸው ጨለመ። ኢትዮጵያ በቁርጥ ቀን ልጆቿ ትላንት የነበራትን የጀግንነት ወኔን ይዛ በአይነቱ ልዩ የሆነ ስኬታማ ምርጫ ማካሄድ ችላለች።
በዚህም ኢትዮጵያ የምትፈልገው ነገር ግን ጠላቶቿ የማይፈልጉት መንግስት ተመስርቷል። የተለያዩ የአፍሪካ ሀገራት መሪዎች ደግሞ በመንግስት ምስረታ መርሃ ግብር ላይ ተገኝተው በመታደም "የእናታቸውን ሳቅ" ለዓለም አስተጋብተዋል።
ወደ ኢትዮጵያ ዝር ማለት አይቻልም፤ ተወራለች፤ ፈርሳለች፤ አዲስ አበባ የጦርነት ቀጠና ልትሆን ነው ብለው ማንም እንዳይገባባት የክልከላ ነጋሪት በማዲያቸው ሲጎስሙ ሚሊዮኖቹ የኢትዮጵያ ዳያስፖራዎች ወደ ሀገር ቤት መጥተው ከሰሜን እስከ ደቡብ፣ ከምስራቅ እስከ ምዕራብ ተንሸራሽረው የጠላት የሀሰት ዜናን በተግባር ውድቅ አድርገዋል።
ገናን በላልይበላ፤ ጥምቀትን በጎንደር በድምቀት በአብሮነት አክብረው ዓለምን ከማስገረም ባለፈ አስደምመዋል። ዓለም አቀፉ በዓል-ጥምቀት ሰላም አይደለችም በተባለችው ኢትዮጵያ ከጫፍ እስከ ጫፍ በድምቀት ተከብሯል።
በተመሳሳይ ከኢድ እስከ ኢድ በሚል የተዘጋጀው የዳያስፖራው የሀገር ቤት ጉዞ የኢድ አል ፈጥርን በዓል በደማቅ ሲያከብሩ ታላቅ የጎዳና የአፍጥር መርሃ ግብር በጠላትና ወዳጅ ዓይን ውስጥ ያረፈ ሀገራዊ ክስተት ሆኖ አልፏል።
አዎ ኢትዮጵያ ዛሬም ሰላም ነች፤ ከሰላምም ሳቅ ላይ ነች። የገጠማት ፈተና የስኬት ውጣ ውረድ አንዱ አካል ነውና ጎትቶ ወደ ኋላ ሊያስቀራት፣ አንገቷን አስደፍቶ ሀዘን ሊያከናንባት አልቻለም፤ ይልቁንም ለደማቅ ሳቋ ምንጭ ሆናት እንጂ። የውጭ ሀገር ጠላት በኢትዮጵያ ላይ ድብቅ ጦሩን እንዲመዝ ካደረጉ ጉዳዮች አንዱ ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ መሆኑ ግልጽ ነው።
እነሱ የበላይ ኢትዮጵያ ደግሞ የበታችና ለማኝ ሆና እንድትኖር ስለሚሹ የለውጥ እና ዕድገት መሰላል ይሆንላታል የተባለው ግድቡ እንዲሰራ አይፈልጉም፤ ውሃ እንዳይሞላ ከካይሮ እስከ ዓለም አቀፉ የፀጥታው ምክር መከሩ።
ሆኖም ስመ ገናና እና የድል አድራጊነት ታሪክ ባለቤት ኢትዮጵያ በሚደረግባት ጫና ሁሉ ሳታጎበድድ ለሦስተኛ ጊዜ ውሃ ሞልታ በግድቡ አናት እንዲፈስ አድርጋ፣ የነገን ብርሃናዊ ተስፋ የፈነጠቀ ሳቅ ስቃለች።
ከዚሁ የጠላት ዓይን ከበዛበት ግድብ በሁለት ዙር ሃይል እንዲያመነጭ በማድረግ ጥልቅ ሀሴት አድርጋለች። እየጠነከሩ እንጂ እየላሉ መሄድ እንደማይስማማትም በተግባር ጭምር አረጋገጠች። ጠላት ዓይኑ እየቀላ ዓባይ ግድቡን ሞልቶ ብርሃንን አመነጨ።
ኢትዮጵያ ትበተናለች ሲባል አንድ ሆና በእነዚህ ውጤቶች ደምቃ የታየችበት ዓመት ነበር በፈተና ታጅቦ ያለፈው የ2014 ዓመት። ጀግኖች ልጆቿ በጦርነት አንድ ሆነው በልማቱ ተባብረው አሁንም ስሟን በደማቅ እየጻፉ ይገኛሉ።
አረንጓዴ፣ ቢጫ፣ ቀይ ሰንደቅ ከምድሯ እንዲጠፉ የሚሯሯጡ ተኩላዎች በሞሉበት በእዚህ ወቅት ሰንደቋ በዓለም ዓቀፍ መድረክ ተውለበለበ፤ ከፍ ብሎም ታየ።
ጦርነትን በግንባር ብቻ ሳይሆን ባሉበት የሥራ መስክ ጠንክሮ በመስራት ግንባር የገጠሙ ልጆቿ ድል ኩራት ሆኗታል። ለአብነትም በአትሌቲክስ ዘርፍ የተሰለፉት ልጆቿ ባመጡት ድል በኦሪገን ሰማይ ስር ኢትዮጵያ ባንዲራዋ ደምቆ ታይቷል።
ከጦርነት ነጻ የሆኑም ሆነ ለኢትዮጵያ መወጋት ጦር የሚያቀብሉ ሁሉ ሰንደቃቸው ከኢትዮጵያ ዝቅ ብሎ ታይቷል። ይህ ለኢትዮጵያ ጮክ ያለ ሳቅን እጅ ነስቶ የጠላትን ቅስም ሰብሯል።
የኦሪገን ምድር የኢትዮጵያውን የመደጋገፍ ጠንካራ እሴት በአትለቶቻችን አማካኝነት ጎልቶ የታየበት ነው። ለዚህም ኢትዮጵያ የደከሙላትን አመስግና በአዲስ አበባ ምድር ሳቋን አጣጥማለች።
ኢትዮጵያ ከለውጡ በኋላ በአራት ዓመት 20 ቢሊዮን ችግኝ የመትከል ግብ ይዛ በተነሳችበት የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ከ25 ቢሊዮን በላይ ችግኝ መትከል የቻለችው በዚሁ ፈታኝ ጊዜ ውስጥ ሆና ነው።
በስንዴ ራስን ለመቻል የተደረገው የበጋ መስኖ ስንዴ ከፍተኛ ሀገራዊ ውጤት ለማስመዝገብ ፍንጭ የታየበት በዚሁ ችግር በተፈራረቀበት ወቅት ነው።
ሌላኛው የኢኮኖሚ ጦርነት የኢትዮጵያን ጉልበት እንዲያብረከርክ ታስቦ ቢሰራም "ምግቤን ከጓሮዬ" እና የከተማ ግብርና ዘመቻዎች ንቅናቄ የተካሄደው የኢትዮጵያን መከራ ማብዣ ሴራ ባየለበት ዓመት ነው።
መከራ ይመጣል መከራ ይሄዳል ኢትዮጵያ ግን ፊቷ እያበራ ነገን ትመለከታለች። ነገን የሚመለከቱ የተስፋ ይኖቿ ብርታትና እገዛ ዛሬ አንድ ብሎ በተጀመረው የ2015 አዲስ ዓመትም የጠላት ክንድ እያደቀቀ ገስጋሴዋ ይቀጥላል። የጠላትን አንገት የሚያስደፋ ሌላ ሳቅ ሌላ ደስታ ነገም በኢትዮጵያ ምድር ይኖራል።
እድሜ ካልን ሁሉን እናያለን...!
ሀገሬ ለዘለዓለም ትሳቅ!
መልካም አዲስ ዓመት