ቀጥታ፡

በሀርቡ መጠለያ ለሚገኙ ከ5ሺህ 500 ለሚበልጡ ተፈናቃዮች ማዕድ ማጋራት ተካሄደ

ደሴ መስከረም 1/2015 (ኢዜአ) በፀጥታ ችግር ምክንያት ከተለያዩ አካባቢዎች ተፈናቅለው በሀርቡ መጠለያ ካምፕ ለሚገኙ ከ5ሺህ 500 በላይ ተፈናቃዮች የዘመን መለወጫ በዓልን ምክንያት በማድረግ ማዕድ የማጋራት መርሃግበር ተካሄደ።

በዓሉም ምክንያት በማድረግ ለተፈናቃዮቹ ማዕድ ያጓሩት ኢትዮ ካናዳ ኔትወርክ ለማህበራዊ ድጋፍና አግማስ ኢትዮጵያ በጎ አድራጎት ድርጅቶች በመተባበር ነው።

በማዕድ ማጋራቱ ላይ የኢትዮ ካናዳ ኔትወርክ ለማህበራዊ ድጋፍ ተወካይ ኢንጂነር መቆያ ወንድይራድ "ይህን ክፉ ቀን እርስ በርስ በመተጋገዝና በመደጋገፍ ተቋቁሞ ማለፍ ይገባናል" ገልጸዋል። 

ድርጅቱ ለተፈናቀሉ ወገኖች አብሮነቱን ለማሳየት ዛሬ የምሳ ግብዣ ማድረጉን ጠቁመው፣ በእዚህም ቁጥራቸው ከ5 ሺህ 500 በላይ ለሆኑ ተፈናቃዮች ምሳ በማብላት በዓሉን በአብሮነት እያሳለፉ መሆኑን ተናግረዋል።  

ቀጣይ ተፈናቀዮችን በሚቻለው ሁሉ ለመደገፍ ዝግጁ መሆናቸውን ገልጸው፣ በንጹሃን ላይ እየደረሰ ያለውን ግፍና በደል ለዓልም በማሳወቅ ለኢትዮጵያ ሉአላዊነት መከበር እንደሚሰሩ አረጋግጥዋል።  

የአግማስ ኢትዮጵያ በጎ አድራጎት ድርጅት ሥራ አስኪያጅ ኢንጂነር አብዱሰላም ሽፋው በበኩላቸው፣ ድርጅቱ፣ በግጭት ምክንያት የተጎዱ ዜጎችንና ወላጅ አልባ ሕፃናትን እየደገፈ መሆኑን ገልጸዋል። 

ዛሬም ከኢትዮ ካናዳ ኔትወርክ ጋር በመተባበር ለተፈናቀሉ ወገኖች ምሳ በማብላት በዓሉን በአብሮነት ማክበራቸውን ነው የገለጹት። 

በሀርቡ ጊዚያዊ መጠለያ ካምፕ ከ5ሺህ 500 በላይ ተፈናቃዮች እንዳሉ የገለጹት ደግሞ በደቡብ ወሎ ዞን የሀርቡ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ያሲን አመዴን ናቸው።

ከንቲባው እንዳሉት መንግስት ለተፈናቀሉ ወገኖች ህብረተሰቡን፣ ባለሀብቱን፣ ዳያስፖራውንና ሌሎችን በማስተባበር የዕለት ደራሽ ምግብና ቁሳቁስ እያቀረበ ነው። 

ዛሬ የተፈናቀሉ ወገኖች በዓልን ተደስተው እንዲያሳልፉ የማዕድ ማጋርት መካሄዱ የቆየውን የኢትዮጵየዊያን የመደጋገፍ፣ የመተጋገዝና የአብሮነት ባህልን ያጠናክራል" ብለዋል። 

እንደዛሬው ለተጎዱ ወገኖች በሚቻለው አቅም አጋርነትና አብሮነትን ማሳየት እንደሚገባ የገለጹት አቶ ያሲን፣ ሁሉም ተፈናቃዮችንና አቅመ ደካሞችን በማገዝ ሀገራዊ ኃላፊነቱን እንዲወጣ አስገንዝበዋል። 

ከተፈናቃዮች መካከል አቶ መሃመድ አወል ኢትዮጵያን ለማፍረስ በተነሱ የጥፋት ኃይሎች ከሞቀ ቤት ንብረታቸው ተፈናቅለው በሀርቡ መጠለያ ካምፕ ለመኖር መገደዳቸውን ተናግረዋል። 

በጥፋት ሀይሎች ባለቤታቸውና አንድ ልጃቸው በአሰቃቂ ሁኔታ መገደላቸውንም ገልጸዋል። 

"እኛም የዘመን መለወጫ ብዓልን እንደሌሎች ደግሰን፣ የተቸገረን ደግፈንና አብልተን እናሳልፈው ነበር ያሉት" አቶ ሰይድ፣ "የገጠመንን ፈተና ተደጋግፈን በማለፍ ኢትዮጵያ ማስቀጠል ይኖርብናል" ብለዋል። 

ዛሬ በዓሉን በጋራ ማሳለፋቸው ባይተዋር እንዳንሆንና ወገን አለን ብለን እንድናስብ አድርጎናል" ያሉት አቶ መሀመድ፣ መንግስት በሀገሪቱ ዘላቂ ሰላምን በማምጣት ወደቄያቸው እንዲመልሳቸውና እንዲያቋቁማቸው ጠይቀዋል።  

"በዓሉን ሳናስበው በደስታ እንድናሳልፍ ላደረጉን ሁሉ እናመሰግናለን፤ የኢትዮጵያ ህዝብ እያደረገልን ላለው የሞራልና የቁሳቁስ ድጋፍ ሁሉ ከብር አለን" ያሉት ደግሞ ሌላዋ ተፈናቃይ ወይዘሮ አንሻ ደጉ ናቸው። 

በተመሳሳይ ዜና የደሴ ከተማ አስተዳደርም ህብረተሰቡንና ባለሃብቱን በማስተባበር የዘመን መለወጫ ብዓልን ከሀገር መከላከያ ሠራዊትና ከአቅመ ደካሞች ጋር በደሴ ከተማ እያከበረ ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም