ያለፈው ዓመት ኢትዮጵያ በብዙ መልኩ ይደርስባት የነበረውን ጫና በጽናትና ትብብር መክታ ያለፈችበት ነበር-- አምበሳደር ጥሩነህ ዜና - ኢዜአ አማርኛ
ያለፈው ዓመት ኢትዮጵያ በብዙ መልኩ ይደርስባት የነበረውን ጫና በጽናትና ትብብር መክታ ያለፈችበት ነበር-- አምበሳደር ጥሩነህ ዜና
አዲስ አበባ መስከረም 1 /2015 (ኢዜአ) በ2014 ዓ.ም ኢትዮጵያ በብዙ መልኩ ይደርስባት የነበረውን ጫና በጽናትና ትብብር መክታ ያለፈችበት ዓመት ነበር ሲሉ አምባሳደር ጥሩነህ ዜና ተናገሩ፡፡
አምባሳደር ጥሩነህ በ2014 ዓ.ም በአትዮጵያ በዲፕሎማሲው መስክና የውስጥ ጉዳዮችን ጨምሮ ሌሎች ጥቅል ጉዳዮችን በሚመለከት ከኢዜአ ጋር ቆይታ አድርገዋል።
ኢትዮጵያ በተጠናቀቀው ዓመት በበርካታ ውጫዊ ጫናዎችና ውስጣዊ ፈተናዎች የተፈተነችበት ነበር ይላሉ አምባሳደር ጥሩነህ።
በብዙ ፈተናዎች ውስጥ የነበረች ቢሆንም በኢትዮጵያዊያን አብሮነት፣ትብብርና በመንግስት ከፍተኛ ጥረት ችግሮችን እየተሻገረች በርካታ ስኬቶችን ማስመዝገቧ ነው የጠቀሱት።
ኢትዮጵያን የማፍረስ እቅድ ተነድፎ በሰሜን ኢትዮጵያ በወስጥ ጠላት የተከፈተባትን ጦርነት በመመከት የነበረውን ሂደት አንስተው ከዚህ ጋር ተያይዞ ከውጭና ከውስጥ በርካታ ፈታኝ ሁኔታዎች እንደገጠሟት አስታውሰዋል።
በተጠናቀቀው ዓመት የህዳሴ ግድብን ሁለተኛ ተርባይን ሃይል ማመንጨት ማስጀመና ሶስተኛ ዙር የውሃ ሙሌት ማሳካቷ ትልቅ እመርታና ስኬት መሆኑን ይጠቅሳሉ።
የኢትዮጵያ መንግስት ፍትሃዊ ህግ የማስከበር አካሄድና ሰላም ለማስፈን የነበረው ጽኑ አቋም ታክሎበት ከወዳጅ አገራት ጋር የተፈጠረው ጠንካራ ዲፕሎማሲ ውስብስብ ችግሮችን በጥበብ እንዲታልፍ ማስቻሉንም ጠቅሰዋል።
በተለይም የአንዳንድ የምዕራባዊያን አገራት ጣልቃ ገብነት በእርዳታ ስም እጅ ለመጠምዘዝ ያደረጉትን ሙከራ ኢትዮጵያ ተቋቁማ ያለፈችበት መንገድ የሚደነቅ መሆኑን ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ ግን የትኛውም አይነት ግንኙነት ሉዓላዊነቷን ባከበረ መንግድ መሆን አለበት የሚለው አቋሟ ምዕራባዊያን በኢትዮጵያ ላይ ይዘውት የነበረን የተዛባ ምልከታ መልሰው እንዲፈትሹ ያደረገ የዲፕሎማሲ ስኬት እንደነበር አንስተዋል።
የኢትዮጵያን እውነታ ለማስረዳት በተለያዩ የዓለም አገራት የሚኖሩ ወገኖች የነበራቸው ሚናም የሚደነቅ እንደነበር ነው የጠቀሱት።
ከዲፕሎማሲ ስራ ጎን ለጎን ጠንካራ የአገር መከላከያ ሰራዊት ማደረጀትና ውስጣዊ የህዝብ አንድነት መፍጠር መቻሉ የአትዮጵያን የአለም አቀፍ ተሰሚነት መሻሻሉን ተናግረዋል።
በኢንባሲዎች የተከናወኑ ተግባራት፣ በህዝቡ ዘንድ የተፈጠረው አንድነትና የመከላከያ ሰራዊቱን በዘመናዊ ሁኔታ የማደራጀትና መገንባት መቻሉ ለዲፕሎማሲው ስኬት የራሱ ሚና እንደነበረው ያብራራሉ።
በተያዘው አዲስ ዓመትም በአገር ላይ ሊደርሱ የሚችሉ የውጭ ጫናዎችንና የውስጥ ፈተናዎችን በትብብርና አብሮነት የመመከት ስራ ተጠናክሮ መቀጠል ይኖርበታል ነው ያሉት።
የኢትዮጵያ ሕልውና ተጠብቆ የቆየው በሕዝቡ ጠንካራ ብሔራዊ ስሜትና አንድነት መሆኑን ጠቁመው አዲሱ ትውልድ ይህንኑ ይበል ማጠናከር እንደሚጠበቅበት ገልጸዋል።
አንጋፋው ዲፕሎማት አምባሳደር ጥሩነህ ዜና በዲፕሎማሲው መስክ ኢትዮጵያን ከሶስት አስርት ዓመታት በላይ ያገለገሉት ታላቅ የአገር ባለውለታ መሆናቸው ይታወቃል።