በአዲሱ ዓመት የዜጎችን ሞት፣ ሰቆቃና መፈናቀልን ለማስቆም መስራት ይገባል--በአፋር የሃይማኖት አባቶች - ኢዜአ አማርኛ
በአዲሱ ዓመት የዜጎችን ሞት፣ ሰቆቃና መፈናቀልን ለማስቆም መስራት ይገባል--በአፋር የሃይማኖት አባቶች
ሰመራ መስከረም 1/2015 (ኢዜአ) በአዲሱ ዓመት የሰላም አማራጮችን በማጠናከርና ለሰላም ተግቶ በመስራት የዜጎችን ሞት፣ ሰቆቃና መፈናቀል ለማስቆም በትኩረት መስራት እንደሚገባ በአፋር ክልል የሃይማኖት አባቶች ገለጹ።
የትግራይ ህዝብ ከሌሎች የኢትዮጵያ ወንድም ህዝቦች ጋር ቁርሾ ውስጥ ከቶ ሊያለያየው እየጣረ ያለውን አሸባሪ ህወሓት በአዲሱ ዓመት በቃህ ብሎ በመቆራረጥ ሰላም ፈላጊነቱን በተግባር ማሳየት እንዳለበትም አመልክተዋል።
የአፋር ክልል እስልምና ጉዳዮች ምክትል ፕሬዚዳንት ሀጂ መሀመድ ደርሳ እንደገለጹት፣ አዲሱ ዓመት የሰላም፣ የፍቅር፣ የመከባበርና የአንደነት እንዲሆን ሁሉም ዜጋ የድርሻውን ማበርከት ይኖርበታል።
ዛሬ በተጀመረው አዲስ ዓመት ዓምና የተስተዋለው የዜጎች ሞት፣ ሰቆቃና መፈናቀልን ለማስቆም ህዝቡ ከምንም በላይ ለሰላም ቅድሚያ ሰጥቶ መስራት እንዳለበት አስግንዝበዋል።
የሀገር ሽማግሌዎች ፣ ፖለቲከኞች፣ ምሁራንና የማህበረሰብ አንቂዎች ህዝብን ከሚያለያይ ይልቅ አንድነትን በሚያጎለብቱ ጉዳዮች ላይ በማተኮር የንጹሀንን ሰቆቃና ሞት ሊያስቀሩ እንደሚገባ ተናግረዋል።
ህዝቡ አብሮነቱን፣ መደጋገፍና ወንድማማችነቱን በማጎልበት ሰላም እንዲያሰፍን እንደሃይማኖት አባት በአዲሱ ዓመት ትኩረት ሰጥተው እንደሚሰሩ ሀጂ መሀመድ ገልጽዋል።
ወንድም የትግራይ ህዝብ በአሸባሪው ህወሓት እየደረሰበት ያለው መከራና ሰቆቃ በአዲሱ ዓመት እንዲያበቃ ሁሉም የበኩሉን ጥረት እንዲያደርግ ጠይቀዋል።
በተለይ የትግራይ ፖለቲከኞች "ትግራይ ተደፈረች" የሚልና መሰል የሀሰት ትርክቶችን በመንዛት ህዝቡን ማብቂያ ለሌው እልቂት ከመማገድ ታቅበው ሰላምን እንዲያስቀድሙ ነው የጠየቁት።
የትግራይ ህዝብ የፓለቲከኞች መጠቀሚያ መሆኑን ትቶ ከጎረቤትና ወንድም ህዝቦች ጋር በሰላም የሚኖርበትን መንገድ መምረጥ እንዳለበትም በመምከር።
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን የአፋር ሀገረ-ስብክት የኦዲትና የቁጥጥር ክፍል ሃላፊ ርዕሰደብር ሰለሞን ሃይሌ በበኩላቸው "አዲሱ ዓመት ዓምና በሰላም እጦት የተከሰተው የዜጎች ሞትና መፈናቀል እንዲቆም ሁላችንም ጠንክረን ሰርተን ውጤት የምናይበት ዓመት መሆን አለበት" ብለዋል።
በተለይ እንደ የሃይማኖት አባት ለሰላም ከመጸለይና ምዕመኑን ከማስተማር ባለፈ የተጣሉትን በማስታረቅ ለሀገር ሰላም ገምቢ ሚናቸውን ለመወጣት ዝግጁ መሆናቸውን ነው የገለጹት።
አንዳንድ አካላት ጥላቻና ግጭትን ከመቀስቀስ ታቅበው እውቀታቸውን ለህዝቦች አብሮነትና ሰላም እንዲሁም ለሀገር ከፍታ በሚጠቅም መልኩ ማዋል እንዳለባቸውም ነው የመከሩት።
ርዕሰደብር ሰለሞን እንዳሉት የትግራይ ህዝብ ከወንድሙ የኢትዮጵያ ህዝብ ጋር ቁርሾ ውስጥ እየከተተው ያለውን ህወሓት በአዲሱ ዓመት በቃህ ብሎ ሰላም ፈላጊነቱን በተግባር ጭምር ማረጋገጥ ይኖርበታል።
በኢትዮጵያ ወንጌላዊት ቤተክርስቲያን የሰመራ-ሎግያ ከተማ ቤተክርስቲያን ዋና ጸሐፊ መጋቢ ሰለሞን እሸቱ "ከውስጥና ከውጭም አየገጠሙ ያሉ ፈተናዎችን በአሸናፊነት ለመወጣት ለአንድ ዓላማ በአንድነት መቆም አለብን" ብለዋል።
በአዲሱ ዓመት "እኔ ብቻ ልሰማ ፤የእኔ ካልሆነ ከሚል መጥፎ መንፈስ ተላቆ በቅንነትና በይቅርባይነት ተቀራርቦ ችግሮችን በመፍታት ሰላምን ለማምጣት መስራት አለብን" ሲሊ መክረዋል።
ለዚህም የትግራይ ህዝብን ጨምሮ ሁሉም ኢትዮጵያዊ ከስሜታዊነት ወጥተው ነገሮችን በሰከነ መንገድ በማየት የመፍትሄው አካል መሆን ይኖርበታል" ብለዋል።
የሃይማኖት አባቶቹ አዲሱ ዓመት ሀገራዊ ችግሮች ሁሉ ተፈተው የህዝብ ሰላምና አብሮነት ደምቆ የሚታይበትና ተጨማሪ የልማት ስኬቶች የሚመዘገቡበት ዓመት እንዲሆን መልካም ምኞታቸውን ገልጸዋል።