ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ የአፍሪካ ሕብረትን የሰላም ሂደት መደገፍ ይኖርበታል- አምባሳደር ነቢያት ጌታቸው - ኢዜአ አማርኛ
ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ የአፍሪካ ሕብረትን የሰላም ሂደት መደገፍ ይኖርበታል- አምባሳደር ነቢያት ጌታቸው
መስከረም 1 /2015 (ኢዜአ) ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ የአፍሪካ ሕብረትን የሰላም ሂደት ውጤታማ እንዲሆን ድጋፍ ማድረግ እንደሚጠበቅበት በአልጄሪያ የኢትዮጵያ አምባሳደር ነቢያት ጌታቸው ገለጹ።
መንግስት አሸባሪው ሕወሓት የሕብረቱን ሚና ለማንኳሰስ እያደረገ ያለውን ጥረት በጽኑ ያወግዛል ብለዋል።
በአልጄሪያ የኢትዮጵያ አምባሳደር ነቢያት ጌታቸው በአገራቱ የሁለትዮሽ ግንኙነትና በወቅታዊ ሁኔታዎች ዙሪያ ከሬዲዮ አልጄሪያ ኢንተርናሽናል ጋር ቆይታ አድርገዋል።
አሸባሪው ሕወሓት መንግስት ለሰላም ሂደቱ እድል ለመስጠትና የሰብአዊ ድጋፍ ተደራሽነት ለማሳለጥ ያወጀውን የሰብአዊ ተኩስ አቁም በመጣስ ዳግም ጦርነት መክፈቱን አምባሳደር ነቢያት ገልጸዋል።
የሽብር ቡድኑ የከፈተው ጦርነት በአማራ፣አፋርና ትግራይ ክልሎች ለሚገኙ ወገኖች የሰብአዊ ድጋፍ ለማድረስ እንቅፋት መፍጠሩንና ተናግረዋል።መንግስት የአፍሪካ ሕብረት የአፍሪካ ቀንድ ልዑክ ኦሊሴጉን ኦባሳንጆ ሰላም ለማምጣት እያደረጉትን ያለውን ጥረት ፍሬያማ እንዲሆን ድጋፍ እያደረገ ይገኛል ብለዋል።
ይሁንና አሸባሪው ሕወሓት የአፍሪካ ሕብረትን ሚና በማንኳሰስና በማጣጣል እየፈጸመ ያለው ተግባር አሳፋሪና በጽኑ የሚወገዝ መሆኑን ነው አምባሳደሩ የገለጹት።
ኢትዮጵያ ለአፍሪካ ችግሮች የአፍሪካ መፍትሔ በሚለው መርህ ላይ የማያወላውል አቋም እንዳላትና የሰላም ሂደቱ በሕብረቱ ማዕቀፍ ይሳካል የሚል እምነት እንዳላት አመልክተዋል።
“ለአፍሪካ ችግሮች አፍሪካዊ መፍትሔ አፍሪካ ሕብረት በአህጉሩ የሚከሰቱ ግጭቶችን ለመፍታት የሚጠቀምበት ቁልፍ የዲፕሎማሲና የፖለቲካ መሳሪያ ነው” ብለዋል አምባሳደር ነቢያት።
በዚህ ረገድም ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ በኢትዮጵያ ሰላም እንዲመጣ የናይጄሪያ የቀድሞ ፕሬዝዳንት ኦሊሴጉን ኦባሳንጆ ጥረት በተቻለው አቀም መደገፍ እንደሚገባው ተናግረዋል።
ኢትዮጵያ የዓለም አቀፉ ማህበረሰብ የሰላም ጥረት ድጋፍ የምትቀበለው በአፍሪካ ሕብረት ማዕቀፍ ብቻ ነው ያሉት አምባሳደሩ ከዛ ውጪ የሚደረጉ እንቅስቃሴዎች ለሰላም የማይበጁና ነገሮችን የሚያወሳስቡ መሆናቸውን አስገንዝበዋል።