የንግዱ ማህበረሰብ ከቀረጥ ነጻ ስምምነቱ ላይ እየተወያየ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የንግዱ ማህበረሰብ ከቀረጥ ነጻ ስምምነቱ ላይ እየተወያየ ነው
አዲስ አበባ ግንቦት11/2010 የአፍሪካ አገራት ከቀረጥ ነፃ ለመገበያየት የደረሱበት የንግድ ስምምነት ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቀርቦ ከመፅደቁ በፊት ከንግዱ ማህበረሰብ ጋር ውይይት እየተካሄደ መሆኑ ተገለፀ። ውይይቱ ኢንዱስትሪዎች ቀድመው እንዲዘጋጁና ከቀረጥ ነፃ ዕድሉ የማይመለከታቸው 15 በመቶ ምርቶች የትኞቹ ይሁኑ ለሚለው ግብዓት እንደሚሆን ተገልጿል። የአፍሪካ አገራት መሪዎች የአህጉሪቱን የነጻ የንግድ ቀጣና ለመመስረት ስምምነት ላይ የደረሱት እንደ አውሮጳውያን አቆጣጠር በ2012 ነበር። መጋቢት 12 ቀን 2010 ዓም ደግሞ ሩዋንዳ ኪጋሊ ላይ 44 የአፍሪካ አገራት የእርስ በእርስ ንግዳቸውን ለማቀላጠፍ ከቀረጥ ነፃ ለመገበያየት የሚያስችላቸውን ስምምነት ተፈራርመዋል። ስምምነቱ ወደ ተግባር የሚገባው ቢያንስ 22 አገራት ከህጋቸው ጋር አጣጥመው በመንግስታቸው ሲፀድቅ ብቻ ነው። እስካሁን ባለው ሁኔታ ጋና፣ ኬንያ፣ ሩዋንዳና ኒጀር ስምምነቱን ለመተግበር ዝግጁ መሆናቸውን ለአፍሪካ ህብረት አስታውቀዋል። ኢትዮጵያም የስምምነቱን ጠቀሜታ ከተረዱ አገራት አንዷ በመሆኗ ስምምነቱ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ከመጽደቁ በፊት ከኢንዱስትሪ ባለኃብቶች ጋር ውይይት እየተደረገበት መሆኑን የንግድ ሚኒስቴር ገልጿል። በሚኒስቴሩ የመልቲ ላተራል ንግድ ግንኙነትና ድርድር ዳይሬክተር እና የኢትዮጵያ ረዳት ተደራዳሪ አቶ ሙሴ ምንዳዬ ለኢዜአ እንደገለፁት 37 አገራት ከ5 ሺህ 601 አይነት ምርቶች መካከል 90 በመቶዎቹን ያለቀረጥ ለመገበያየት ሲስማሙ ኢትዮጵያን ጨምሮ ሰባት አገራት ደግሞ 85 በመቶዎቹን ብቻ ከቀረጥ ነፃ ለመገበያየት ተስማምተዋል። ኢትዮጵያ በዚህ ስምምነት በመታገዝ የውጭ ባለሃብቶችን ለመሳብ ከመቻሏ በተጨማሪ እየተስፋፉ ለመጡት የኢንዱስትሪ ፓርኮች የገበያ ዕድል ለመፍጠር ከፍተኛ አስተዋፅኦ ይኖራቸዋል ብለዋል። በአንፃሩ ምርቶች ከቀረጥ ነፃ ሲገቡ ቀደም ሲል ከቀረጥ ሲገኝ የነበረው ገቢ ሊቀንስ እንደሚችልና ኢንዱስትሪዎች ካልተጠናከሩ በውድድሩ ጫና ሊፈጠርባቸው እንደሚችል ይገልፃሉ። ኢንዱስትሪዎች ከወዲሁ ከሌሎች የአፍሪካ አቻዎቻቸው ጋር በምርቶቻቸው ጥራትና ብዛት ተወዳዳሪ እንዲሆኑ ለማዘጋጀት ስምምነቱ ከመፅደቁ በፊት ከንግዱ ማህበረሰብ ጋር ውይይት እየተደረገበት መሆኑን ገልፀዋል። መንግስት የራሱ ፖሊሲ ቢኖረውም 15 በመቶዎቹ ከቀረጥ ነፃ መሆን ያለባቸው ምርቶች የትኞቹ ይሁኑ የሚለውን ለመወሰን እና ወደፊት ለሚደረጉ ድርድሮች ከነጋዴዎች የሚነሱ ሃሳቦችን በግብዓትነት እንደሚጠቀም ገልፀዋል። ውይይቱ ሲጠናቀቅም የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንዲያጸድቀው ይቀርባል ነው ያሉት። ኢትዮጵያ በአፍሪካ አገራት ምርቶቿን በመላክ ያላት የገበያ ድርሻ 20 በመቶ ሲሆን ከአገራቱ የምታስገባው ምርት ደግሞ አራት በመቶ መሆኑን አቶ ሙሴ ጠቁመዋል። ነጻ የንግድ ቀጣና ስምምነቱ እንደ አውሮጳውያን አቆጣጠር በ2020 የአህጉሪቱን አገራት የንግድ ልውውጥ በ52 በመቶ እንደሚጨምረው የአፍሪካ የኢኮኖሚ ኮሚሽን መረጃ ያመለክታል።