ቀጥታ፡

አንድነት በዜጎች ህይወት ላይ ተጨባጭ ለውጥ ማምጣት እንደሚችል መቄዶንያ ሁነኛ ማሳያ ነው -አቶ ቢኒያም በለጠ

ጷጉሜን 5/2014/ኢዜአ/ አንድነት በዜጎች ህይወት ላይ ተጨባጭ ለውጥ ማምጣት እንደሚችል መቄዶንያ የአረጋውያንና የአእምሮ ህሙማን መርጃ ማዕከል ሁነኛ ማሳያ ሊሆን እንደሚችል የማዕከሉ መስራችና ስራ አስኪያጅ ቢኒያም በለጠ ገለጹ።

''ሰውን ለመርዳት ሰው መሆን በቂ ነው'' በሚል መርህ የተመሰረተው የመቄዶንያ አረጋውያንና የአእምሮ ህሙማን መርጃ ማዕከል፤ አንድነትና ትብብር ዋነኛ መገለጫው መሆኑን የማዕከሉ መስራች ቢኒያም በለጠ ከኢዜአ ጋር ባደረጉት ቆይታ ተናግረዋል፡፡

በዚህም ማዕከሉ በዋናነት ለችግር የተጋለጡና ጧሪ አልባ አረጋዊያንና የአእምሮ ህሙማንን እያገዘ መሆኑን ጠቅሰው፤ ለዚህ ደግሞ ማእከሉ ከበጎ ፈቃደኞች ጋር በጋራ እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡  

''ሰውን ለመርዳት ሰው መሆን በቂ ነው'' በሚለው የማእከሉ መርህ አማካኝነትም ሁሉም ኢትዮጵያዊ ያለ ሃይማኖትና ማንነት ልዩነት በአንድነት ለማዕከሉ ድጋፍ እያደረጉ ነው፤ ይህም በተጨባጭ በዜጎች ህይወት ላይ ለውጥ ማምጣት አስችሏል ነው ያሉት፡፡

ማዕከሉ የተለያዩ የሃይማኖት ተከታዮችና ከተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች የመጡ ብሔር ብሔረሰቦች  በፍቅርና በአንድነት የሚኖሩበት ነው።

በማዕከሉ ለሁሉም የእምነት ተከታዮች የየራሳቸው የሆነ ቤተ እምነቶች እንዳሏቸው ጠቁመው የአምልኮ ስርዓታቸውንም ሆነ ሃይማኖታዊ በዓላቸውን በመከባበርና በመቻቻል  እንደሚያከብሩ ነው የገለጹት።

በተጨማሪም ሌሎች አገልግሎቶችንም እንዲሁ በጋራ የሚጠቀሙ ሲሆን 'በማዕከሉ ማንም የበላይ ማንም የበታች የለም' ያሉት አቶ ቢኒያም፤ የጠነከረ መተባበርና ፍቅር እንዲሁም የአንድነት ስሜት አለ ብለዋል።

መቄዶንያ የተቋቋመበትን ዓላማ ከማሳካት አኳያ በማዕከሉ የሰረጸው የአንድነት ስሜት ትልቅ ሚና እንዳለው በመጠቆም።

ከጎዳና ተነስተው በማዕከሉ ድጋፍ ከነበሩበት ችግር አገግመው ሀጅ አድርገው የመጡ ሙስሊሞች ኢየሩሳሌም ተሳልመው የመጡ ክርስቲያኖች በማዕከሉ ውስጥ መኖራቸውን ጠቅሰዋል።

አንድነትን በማጎልበት በዜጎች ህይወት ላይ ተጨባጭ ለውጥ ማምጣት እንደሚቻልም መቄዶንያ የአረጋውያንና የአዕምሮ ህሙማን መርጃ ማዕከል ሁነኛ ማሳያ ተደርጎ ሊወሰድ እንደሚችል አብራርተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም