"አንድነት ኢትዮጵያ የቆመችበት አለት ነው" --ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን - ኢዜአ አማርኛ
"አንድነት ኢትዮጵያ የቆመችበት አለት ነው" --ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን
ጳጉሜን 05 ቀን 2014 (ኢዜአ) "አንድነት ኢትዮጵያ የቆመችበት አለት ነው" ሲሉ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ተናገሩ።
የመከላከያ ሚኒስቴር የአንድነት ቀንን "ስናብር ስናምር" በሚል መሪ ቃል በተለያዩ መርሃ ግብሮች እያከበረ ይገኛል።
በመርሃ ግብሩ የተገኙት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ኢትዮጵያ በብዝሃነት ውስጥ ያለ አንድነቷን ስታጠናክር ውበቱ ጥልቅና የጎላ ነው ብለዋል።
"አንድነት ኢትዮጵያ የቆመችበት አለት ነው" ሲሉም የኢትዮጵያውያንን የአንድነት ኃይል በአፅንኦት አንስተዋል።
የጠንካራ ሀገር የውጭ ግንኙነት መሰረቱ ጠንካራ ውስጣዊ አንድነት መሆኑን በመጥቀስ ኢትዮጵያውያንም ውስጣዊ አንድነታቸውን ማጠንከር እንዳለባቸው ተናግረዋል።
"አንድነት ውርሳችን፣ ምግባራችን፣ የመጪው ዘመን ህልማችን እውን መሆን ማረጋገጫ ቁልፍ መሳሪያችን ነው" ብለዋል።
የኢትዮጵያውያንን አንድነት እኛ ብቻ ሳንሆን ዓለም በጥብቅ የሚረዳው የአኩሪ ብሔራዊ ድሎቻችን መሰረት መሆኑንም እንዲሁ።
መንግስት የሀገር ክብርና አንድነትን ለማስጠበቅ ከመቼውም ጊዜ በላይ ጠንክሮ መምራትና ማስተባበርን እውን እያደረገ እንደሚገኝ ገልጸዋል።
የመከላከያ ሚኒስትሩ ዶክተር አብርሃም በላይ በበኩላቸው የአንድነት ምሳሌ ከሀገር መከላከያ በላይ የሚገልጽበት ቦታ የለም ነው ያሉት።
ባለፉት አራት ዓመታት መከላከያ ሠራዊት ከፓርቲ መሳሪያነት ወጥቶ የሀገርና ህዝብ መከታ ሆኖ እንዲገነባ መደረጉንም ተናግረዋል።
የአንድነት ቀን ዛሬ በመላው ሀገሪቱ በተለያዩ መርሃ ግብሮች እየተከበረ ይገኛል።