ኢትዮ ቴሌኮም መንግሥታዊ ካልሆነ ድርጅት ጋር በመተባበር ለችግረኛ ቤተሰብ ተማሪዎች ድጋፍ አደረገ - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮ ቴሌኮም መንግሥታዊ ካልሆነ ድርጅት ጋር በመተባበር ለችግረኛ ቤተሰብ ተማሪዎች ድጋፍ አደረገ
ነቀምቴ/ጂንካ ጳጉሜን 05/2014/ኢዜአ/ኢትዮ ቴሌኮም ምዕራብ ሪጅን ከኦሮሚያ የወንድማማቾች ዕርዳታና አንድነት መንግሥታዊ ያልሆነ አገር በቀል ድርጅት ጋር በመተባበር ለችግረኛ ተማሪዎች የትምህርት መሣሪያዎችን ድጋፍ ማድረጉን አስታወቀ፡፡
የሪጂኑ ዋና ዳይሬክተር አቶ ሙላቱ ጉደታ እንዳስታወቁት ለ6 ሺህ ተማሪዎች የትምህርት መሣሪያዎች ድጋፍ ይደረጋል፡፡
የመጀመሪያውን ድጋፍ በምሥራቅ ወለጋ ዞን የፀባይ ማረሚያ ቤት በሚገኘው የድሬ ጃቶ 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ለሚገኙ ለ552 ችግረኛ ቤተሰብ ተማሪዎች በ469 ሺህ 800 ብር የሚገመት የደብተር ድጋፍ መደረጉን አመልክተዋል።
የኦሮሚያ የወንድማማቾች ዕርዳታና አንድነት መንግሥታዊ ያልሆነ አገር በቀል ድርጅት አስተባባሪ አቶ ተመስገን ሽሜ በበኩላቸው ድርጅቱ የተቋቋመለትን ዓላማ ለማሳካት ከኢትዮ ቴሌኮም ምዕራብ ሪጂን ጋር በመተባበር 522 ደርዘን ደብተሮችን ድጋፍ ማድረጉን ተናግረዋል፡፡
የነቀምቴ ከተማ የሴቶችና ሕፃናት ጉዳይ ጽህፈት ቤት ኃላፊ ወይዘሮ ትግሥት ቦጄ ስለተደረገው ድጋፍ አመስግነው በማረሚያ ቤት ሆነው ትምህርታቸውን በመከታተል ላይ የሚገኙ ተማሪዎች በድጋፉ በመበረታታት ትምህርታቸውን ጠንክረው መማር እንዳለባቸው አሳስበዋል፡፡
በማረሚያ ቤቱ ትምህርታቸውን እየተከታተሉ ያሉ ተማሪዎች በተደረገላቸው ድጋፍ አመስግነዋል፡፡
በተመሳሳይ ኢትዮ-ቴሌኮም በጂንካ ከተማ ለሚገኙ ከ500 በላይ ለሚሆኑ ድጋፍ ለሚሹ ተማሪዎች ከግማሽ ሚሊዮን ብር በላይ የዋጋ ግምት ያለው የትምህርት ቁሳቁስ ድጋፍ አድርጓል፡፡