በህዳሴ ግድብ ዙሪያ የሚስተዋሉ የተሳሳቱ አመለካከቶች በቅኝ ግዛት ውል የናይል ወንዝን በብቸኝነት ለመጠቀም ካለ ፍላጎት የሚመነጩ ናቸው - ኢዜአ አማርኛ
በህዳሴ ግድብ ዙሪያ የሚስተዋሉ የተሳሳቱ አመለካከቶች በቅኝ ግዛት ውል የናይል ወንዝን በብቸኝነት ለመጠቀም ካለ ፍላጎት የሚመነጩ ናቸው
ጳጉሜ 5 ቀን 2014 (ኢዜአ) በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ዙሪያ የሚስተዋሉ የተሳሳቱ አመለካከቶች በቅኝ ግዛት ውል የናይል ወንዝን በብቸኝነት ለመጠቀም ካለ ፍላጎት የሚመነጩ ናቸው ሲሉ የግድቡን ፕሮጀክት የጎበኙ የዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ፣ የኬኒያና የደቡብ ሱዳን ልዑክ አባላት ተናገሩ።
ግብፅ የቅኝ ግዛት ዘመን የናይል ወንዝ ስምምነቶችን እንደመከራከሪያ ከማቅረብ ይልቅ በምክንያታዊና ፍትሐዊ የውሃ አጠቃቅም ላይ ወደ አፍሪካዊ መፍትሔ መምጣት እንዳለባትም ገልጸዋል።
የታላቁ የኢትዮጵያ የሕዳሴ ግድብ ፕሮጀክትን በአካል ከጎበኙ የናይል ተፋሰስ ሀገራት ልዑካን መካከል የዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ፣ የኬኒያና የደቡብ ሱዳን ተወካዮች ይገኙበታል።
የሀገራቱ ልዑክ አባላት ለኢዜአ እንዳሉት በኢትዮጵያውያን የራስ አቅም እየተገነባ ያለው ታላቁ የሕዳሴ ግድብ ለቀጣናው ሀገራት ተጠቃሚነት ተስፋ የተጣለበት የአፍሪካ ኩራት የሆነ ፕሮጀክት ነው።
የዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ የውሃና መስኖ ሚኒስትር አማካሪ ኢነጅነር ሮበርት አሙኒ፤ ግድቡ ለአፍሪካውያን በራሳቸው አቅም ለመልማት የይቻላል መንፈስን የሚሰጥ አርዓያ ፕሮጀክት መሆኑን ገልጸዋል።
በላይኛው የተፋሰሱ ሀገራት የሚገኙ የልማት ፕሮጀክቶችን ግብፅን ጨምሮ የታችኛው የተፋሰሱ ሀገራት በስጋትነት እንደሚመለከቷቸው አንስተው፤ ግድቡ ለአፍሪካውያን ከድህነትና ጨለማ የመውጫ ግድብ መሆኑን ማሰብ እንዳለባቸው ነው የጠቀሱት።
የተፋሰሱ ውሃ ሀብት ከድህነት መውጫ በመሆኑ ውሃን በፍትሐዊና ምክንያታዊ አግባብ በውይይት ለጋራ ተጠቃሚነት ማዋል ተገቢ እንደሆነ ገልጸዋል።
የቀድሞ የናይሮቢ ከንቲባና የኢትዮጵየ ኬኒያ ወዳጆች ማኅበር ሊቀመንበር ጆ አኬችና የደቡብ ሱዳን የብሔራዊ ወጣቶች ሕብረት ዋና ፀሐፊ ጀስቲን ኡሪዮ ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ለታችኛው ተፋሰስ ሀገራት ጥቅም እንጂ ጉዳት እንደሌለው ገልጸዋል።
አክለውም ግብጻውያን ግድቡን በአካል መጥተው ቢመለከቱ ምናልባትም ጉዳት እንደማያደርስባቸው ስለሚያረጋግጡ ሊደግፉት እንጂ ሊነቅፉት እንደማይችሉም ነው የተናገሩት።
ግድቡ ግብፅን የህልውና አደጋ አደጋ ውስጥ ይከታል በሚል አንዳንድ ግብጻውያንና በዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ውስጥ ያሉ አካላት የሚነዙት ፕሮፓጋንዳ ፍጹም ከዕውነት የራቀ ስለመሆኑም እንዲሁ።
የዚሁ ትርክት ዋነኛ ባለቤት አፍሪካን እንዳትለማ የሚሹ አካላት መሆናቸውን ጠቅሰዋል።
ኢትዮጵያ ካለማንም ድጋፍ በራሷ አቅም የሃይል ማመንጫ ግድብ መገንባቷ ግብፅንም ሆነ የትኛውንም የታችኛው የተፋሰሱ ሀገር አይጎዳም ያሉት ጎብኚዎቹ፤ የኃይል ማመንጫ ግድቡ የወንዙን ተፈጥሯዊ ፍሰት እንደማያስቀር በዓይናቸው ተመልክተው ማረጋገጣቸውን አንስተዋል።
የናይል ተፋስስ ሀገራት የተፋሰሱ ውሃ ሀብቶችን በምክንያታዊና ፍትሃዊ መልኩ መጠቀም እንደሚገባ ገልጸው፤አለመግባባቶች ካሉም በአፍሪካዊ መፍትሄ ስምምነት ሊደረስባችው ይገባል ነው ያሉት።
ግብፅም ራሷን ከቅኝ ግዛት ዘመን ውሎች አዙሪት ልታወጣ ይገባል ነው ያሉት።
ይልቁኑ የተፋሰሱ ውሃ ሀብቶች የአገራቱን ዜጎች ከድህነት መውጫ መሳሪያ በመሆኑ እንጂ የግጭት መነሻ መሆን እንደሌለባቸው ጠቅሰው፤ በየጊዜው የሚከለሱ ስምምነቶችን በማድረግ በፍትሓዊነት መጠቀም እንደሚገባ ተናግረዋል።
የውሃ አጠቃቀም ውዝግቦች 'ለአፍሪካ ችግሮችን አፍሪካዊ መፍትሔ' በሚለው መርህ እልባት ሊበጅላቸው እንደሚገባና ግብፅም በዚህ ስርዓት ልትራመድ ይገባል ነው ያሉት።