ቀጥታ፡

አዲሱ ዓመት ለሀገራችን ከፍታ የምንተጋበት ዓመት ሊሆን ይገባል -አቶ ርስቱ ይርዳው

ሀዋሳ፣ ጳጉሜ 5 ቀን 2014 (ኢዜአ) አዲሱ ዓመት የኢትዮጵያን ከፍታ ለማረጋገጥ የምንተጋበት ዓመት ሊሆን እንደሚገባ የደቡብ ክልል ርዕሰ-መስተዳድር አቶ ርስቱ ይርዳው ተናገሩ።

የደቡብ ክልል ርዕሰ-መስተዳድር አቶ ርስቱ ይርዳው የ2015 ዓ.ም አዲስ አመትን በማስመልከት የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላለፈዋል።

ርዕሰ-መስተዳድሩ የ2015 ዓ.ም አዲስ አመት በማስመልከት ባስተላለፉት መልዕክት እንደገለጹት አዲሱ ዓመት የሀገራችንን ከፍታ ለማረጋገጥ የምንተጋበት ሊሆን ይገባል፡፡

አዲሱ ዓመት ለኢትዮጵያ የከፍታ፣ ለህዝቦቿ አንድነት እና ዘላቂ ሰላም የሚሰፍንበት ዘመን እንዲሆንም ተመኝተዋል።2014 ዓ.ም በበርካታ ፈተናዎች ውስጥ አልፈን እቅዳችንን በስኬታማነት የፈፀምንበት አመት ነበርም ብለዋል።

ሀገር የማፍረስ ተልዕኮን ያነገበው አሸባሪው ህወሀት በሀገራችን ላይ የሰነዘረውን ወረራ የክልላችን ህዝቦች ከመላው ኢትዮጵያውያን ጋር በመተባበር በመመከት ረገድ ከፍተኛ ሚና መጫወት እንደቻሉም ርዕሰ መስተዳድሩ አብራርተዋል።

በበጀት አመቱ የመንግስት ምስረታውን ውጤታማ ማድረግ ከመቻሉም ባሻገር በግብርና፣ በመሰረተ ልማት እና በኢንቨስትመንት ዘርፎች መላው የክልሉን ህዝብ በማሳተፍ አመርቂ ውጤት ማስመዝገብ ችለናል ብለዋል።

በ2015 የህወሃት የሽብር ቡድን ለሦስተኛ ጊዜ የሰነዘረብንን ጥቃት በአስተማማኝ ሁኔታ የምንመክትበት፣ ኢትዮጵያን የመበተን ህልሙን ቅዠት የምናደርግበት፣ በልማት ግንባሩም ጠንክረን የምንሰራበት ሊሆን ይገባል ብለዋል፡፡

በአጠቃላይ የጠላትን አጀንዳ በመዝጋት ትኩረታችንና ርብርባችንን ልማትና ብልፅግና ላይ የምናደርግ ሊሆን እንደሚገባ ጠቁመዋል።

በክልሉ እስከአሁን ለነበረው አጠቃላይ የህዝብ ሁለንተናዊ ተሳትፎና ድጋፍ ርዕሰ መስተዳድሩ ምስጋና አቅርበዋል።በአዲሱ ዓመትም ይሄው የህዝብ አንድነት፣ መተሳሰብ እና ድጋፍ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ርዕሰ መስተዳድሩ ጥሪ አቅርበዋል።

አዲስ ዓመት በዓል ስናከብር በተለያዩ ምክንያቶች ተፈናቅለው በመጠለያ የሚገኙትንና በአጠገባችን የሚገኙ አቅመ ደካሞችና የተቸገሩ ወገኖቻችንን መርዳትና መጠየቅ እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል።

ርዕሰ መስተዳድሩ በመልዕክታቸው ለመላው የኢትዮጵያ ህዝብ፣ ለሀገር ሰላምና ሉዓላዊነት መከበር በዱር በገደሉ እየተዋደቁ ለሚገኙ የሀገር መከላከያ ሰራዊት፣ ለፖሊስ አባላትና ሚሊሻ ሃይሎች እንኳን ለአዲሱ ዓመት በሰላም አደረሳችሁ ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም