በእርድ ወቅትና ከእርድ በኋላ ለቆዳና ሌጦ ተገቢውን ጥንቃቄ በማድረግ እየደረሰ ያለውን ከፍተኛ ብክነት ማስቅረት ይገባል - ኢዜአ አማርኛ
በእርድ ወቅትና ከእርድ በኋላ ለቆዳና ሌጦ ተገቢውን ጥንቃቄ በማድረግ እየደረሰ ያለውን ከፍተኛ ብክነት ማስቅረት ይገባል
አዲስ አበባ ጳጉሜን 5 / 2014 (ኢዜአ) በእርድ ወቅትና ከእርድ በኋላ ለቆዳና ሌጦ ተገቢውን ጥንቃቄ በማድረግ እየደረሰ ያለውን ከፍተኛ ብክነት ማስቅረት እንደሚገባ ጥሪ ቀረበ፡፡
ሁለተኛ የትግበራ ዓመቱን ባገባደደው የአስር ዓመቱ የልማት ዕቅድ ለአምራች ኢንዱስትሪው ትኩረት መስጠት በቀዳሚነት ከተያዙ የልማት አጀንዳዎች መካከል ይጠቀሳል።
በተለይም እንደ ቆዳ ያሉ የአገር ውስጥ ምርቶችን በጥሬ ዕቃነት ለሚጠቀሙ አምራች ኢንዱስትሪዎች ትኩረት በመስጠት አስተማማኝ የኢንዱስትሪ መሠረት ለመገንባትና ሰፊ የሥራ ዕድል ለመፍጠር እንደሚሰራ በዕቅዱ ተመላክቷል።
ለዚህ ደግሞ ኢትዮጵያ ያላት ከ120 ሚሊዮን የሚበልጥ የእንስሳት ሀብት እንደ መልካም ዕድል የሚወሰድ ነው።
ይሁን እንጂ የእንስሳት ሀብትና የእንስሳት ውጤቶችን በሚፈለገው ልክ ጥቅም ላይ ከማዋል አኳያ ሰፊ ጉድለቶች መኖራቸው ይታወቃል።
ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ ደግሞ በተለይ በበዓላት ወቅት የእርድ እንስሳት ቆዳ በየቦታው ተጥሎ አካባቢ ሲያቆሽሽና ለብክነት ሲዳርግ መመልከት እየተለመደ መጥቷል።
ለዚህ ደግሞ የቆዳ ዋጋ ዝቅተኛ መሆን፣ በተገቢው መልኩ ምርቱን የሚሰበስቡ አካላት አለመኖር፣የግብይት ችግር በምክንያትነት ይጠቀሳሉ።
ኢዜአ ያነጋገራቸው በእንስሳት እርድ ስራ የተሰማሩ ግለሰቦች እንደሚሉት በበዓላት ወቅት በርካታ ዕርድ መኖሩን ጠቅሰው፤ የቆዳ ዋጋ ዝቅተኛ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ ምርቱ ፈላጊ ማጣቱን ገልጸዋል።
በእርድ ወቅት በሚከሰት የጥንቃቄ ጉድለት ምክንያት በርካታ የቆዳ ምርት ለብክነት እየተዳረገ መሆኑም ይገልጻሉ፡፡
በተጨማሪም የቆዳ ፋብሪካዎች ታች ድረስ ወርደው ከቆዳ ሰብሳቢዎችና አቅራቢዎች ጋር በቅንጅት አለመስራት፤እንዲሁም ቆዳን ሳይበላሽ ለማቆየት የሚውሉ ግብዓቶች እጥረት በዘርፉ ከሚስተዋሉ ተግዳሮቶች መካከል ተጠቃሾች ናቸው፡፡
ይህም የቆዳ አንዱስትሪዎች ፍላጎትና የቆዳ አቅርቦት እንዳይጣጣም አድርጓል።
የኢንዱስትሪ ግብአቶች ልማት ድርጅት ምክትል ዋና ስራ አስፈጻሚ ሰለሞን ግርሻ የጨው አቅርቦት እጥረት ለቆዳ ምርት ብክነት ሲዳርግ መቆየቱን ያነሳሉ፡፡
ካለፉት ጊዜያት ልምድ በመውሰድ ለዘንድሮው የዘመን መለወጫ በዓል ከ78 ሺህ ኩንታል በላይ ጨው ለቆዳ ሰብሳቢዎችና አከፋፋዮች መሰራጨቱን ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ ቆዳና ቆዳ ውጤቶች ኢንዱስትሪ ምርምርና ልማት ማዕከል ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክተር ብርሀኑ ተሾመ በበኩላቸው ኢትዮጵያ ያሏት የቆዳ ፋብሪካዎች በዓመት እስከ 50 ሚሊዮን ቆዳና ሌጦ የመጠቀም አቅም እንዳላቸው ተናግረዋል፡፡
ነገር ግን ተገቢውን ጥራት አሟልቶ በዓመት ለኢንዱስትሪዎች የሚቀርበው የቆዳና ሌጦ ምርት ከ23 ሚሊዮን አለመሻገሩን ገልጸዋል።
ይህም የችግሩ መጠን ምን ያህል የጎላ እንደሆነ አመላካች መሆኑን በመጥቀስ፡፡
እርድ በተፈጸመ በተወሰነ ሰአት ውስጥ ቆዳዎችን ሰብስቦ ወደሚፈለገው ቦታ የማድረስ የሎጂስቲክስ ችግር መኖሩ ቆዳዎች በየአካባቢው እንዲባክኑ እያደረገ መሆኑ ተገልጿል።
እያንዳንዱ ቆዳ ከየአካባቢው ተሰብስቦ በኢንዱስትሪው ውስጥ አስፈላጊው እሴት የመጨመር ስራ ከተከናወነ በኋላ ለውጭ ገበያ ቀርቦ ለአገር የሚያስገኘው ኢኮኖሚያዊ ፋይዳ ጉልህ በመሆኑ ህብረተሰቡም ቆዳዎች እንዳይባክኑ የበኩሉን ድርሻ እንዲወጣ ጥሪ አቅርበዋል።