የምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት ኃላፊ የነበሩት የአቶ ዐብይ ኤፍሬም ሥርዓተ ቀብር በቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ተፈጸመ - ኢዜአ አማርኛ
የምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት ኃላፊ የነበሩት የአቶ ዐብይ ኤፍሬም ሥርዓተ ቀብር በቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ተፈጸመ
ጳጉሜን 4 / 2014 (ኢዜአ)የምክትል ጠቅላይ ሚኒስቴር ጽህፈት ቤት ኃላፊ የነበሩት የአቶ ዐብይ ኤፍሬም ሥርዓተ ቀብር በመንበረ ጸባኦት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ቤተክርስቲያን ተፈጸመ።
በሥርዓተ ቀብሩም ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ አቶ ደመቀ መኮንን፣ የፌደሬሽን ምክር ቤት አፈጉባኤ አገኘሁ ተሻገር፣ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ምክትል አፈጉባኤ ሎሚ በዶ ጨምሮ ሌሎች ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች፣ወዳጅ ዘመዶቹና የስራ ባልደረቦቹ በተገኙበት ተፈፅሟል።
አቶ ዐብይ ከአባቱ ከአቶ ኤፍሬም ሞትባይኖር እና ከእናቱ ከወይዘሮ አሰለፍ ተሰማ ነሐሴ 29 ቀን 1974 ዓ.ም በአዲስ አበባ ከተማ እንደተወለደ የህይወት ታሪኩ ያስረዳል።
ወላጅ አባቱ በስራ ምክንያት ወደ መቂ በመዛወራቸው ከ1981 ዓ.ም ጀምሮ የአንደኛና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን በመቂ ከተማ ተከታትለዋል።
በትምህርት አቀባበላቸውም ምስጉን፣የደረጃ ተማሪና በጸባይም ተጨዋች፣ ትሁት፣ሁሉን ወዳድ እንደነበሩ በቅርብ ወዳጅ ዘመዶቻቸው የተመሰከረላቸው አቶ ዐብይ፤ ከህፃንነታቸው ጀምሮ ለስነጽሁፍ የተለየ ፍቅር እንዳለቸው ተገልጿል፡፡
በዚሁ ክህሎታቸውም በ1993 ዓ.ም የኢትዮጵያ ቋንቋዎችና ስነጽህፍ ትምህርት ክፍል የመጀመሪያ ዲግሪ ትምህርታቸውን ለመከታተል በቅተዋል።
ከስነ-ጽሁፍ ትምህርታቸው በተጓዳኝም ከኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ኢንስቲትዩት በጋዜጠኝነት፤ከእስፔኑ የሰብዓዊ ድጋፍ ማዕከል ኢንስቲትዩት በብሔራዊ ኮሙዩኒኬሽን የሁለተኛ ዲግሪያቸውን ተከታትለዋል።
ለስነ-ጹህፍ ካላቸው ተሰጥኦ የተነሳም በመጪው የ2015 ዓ.ም መጽሐፍ በማሳተም ለወዳጅ ዘመዳቸውና ተደራሲያን እንካቹህ ለማለት በዝግጅት ላይ ነበሩ።
ወደስራው ዓለም በመቀላቀልም "ዘ-ሰን" በተሰኘው የእንግሊዝ ጋዜጣ፣ በናሽናል ኮንስትራክሽን መጽሔትና በሌሎች የግል መገናኛ ብዙሃን በመስራት የስነጹህፍና የጋዜጠኝነት ሙያቸውን በብቃት አስመስክረዋል።
በመቀጠልም ከ2001 እስከ 2007 ዓ.ም በሴቶች፣ህፃናትና ወጣቶች ጉዳይ ሚኒስቴር የኮሙዩኒኬሽን ዋና ዳይሬክተር በመሆን አገልግለዋል።ተቋማቸውንም ከክልል መዋቅር እስከ ባለድርሻ አካላትና ማህበረሰቡ ድረስ ስኬታማ ተግባራትን በማከናወን ግንባር ቀደም አመራር በመሆን እውቅና ተችሯቸዋል።
በ2008 ዓ.ም በነበራቸው የተሻለ የስራ አፈፃጸም የምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት የኮሙዩኒኬሽን ዳይሬክተርና የምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ልዩ ረዳት እንዲሁም የጽህፈት ቤቱ ኃላፊ በመሆን ህልፈተ ህይወታቸው እስከተሰማበት ዕለት ድረስ አገልግለዋል።
በዚህ ወቅትም ከምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጎን በመሆን በዓለም አቀፍ መድረኮች ላይ ለኢትዮጵያ ይበጃሉ ያሏቸውን የተሻሉ ሃሳቦች በማዋጣት ለአገራቸው ታሪክ የማይዘነጋው አስተዋጽኦ አበርክተዋል።
አቶ ዐብይ ኤፍሬም በ2007 ዓ.ም ከወይዘሮ ትዕግስት ምስጋናው ጋር በትዳር በመጣመር የአንድ ወንድና ሁለት ሴት ልጆችን ለማፍራት በቅተዋል።
በርካቶች ትሁት፣ ቤተሰብና አገሩን ወዳጅ፣ ትጉህ ሰራተኛና ታማኝ ሲሉ የሚገልጿቸው አቶ ዐብይ ጳጉሜ 02ቀን 2014 ዓ.ም ምሽት በድንገተኛ ህመም በተወለዱ በ40 ዓመታቸው ከዚህ ዓለም በሞት ተለይተዋል።