ቀጥታ፡

ሠራዊታችን ከየትኛውም አቅጣጫ የሚመጣ ጠላትን ለመመከት ዝግጁ ነው -- ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ

ጳጉሜን 4 / 2014 (ኢዜአ) ሠራዊታችን ከየትኛውም አቅጣጫ የሚመጣ ጠላትን ለመመከት የሚያስችል ቁመናና ዝግጁነት አለው ሲሉ የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ አስታወቁ።

የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ በጦር ሃይሎች ጠቅላይ መምሪያ በየሶስት ወሩ እየታተመ በሚወጣው ‘መከታ’ መጽሔት ላይ ለአገር መከላከያ ሰራዊት ለአዲሱ ዓመት የ’እንኳን አደረሳችሁ’ መልዕክት አስተላልፈዋል።

በመልዕክታቸው የተከበራችሁ የኢትዮጵያ ብሄር ብሄረሰቦችና ሕዝቦች እንዲሁም የጀግናው የመከላከያ ሠራዊታችን አመራሮችና አባላት በርካታ ፈተናዎችን በድል አድራጊነት ወደ ተሽጋገርንበት የ2015 አዲስ አመት እንኳን አደረሰን አደረሳችሁ ብለዋል።

ከቀደመው 2013 የተሻገረውን ጨምሮ 2014 ዓ.ም በአንድ በኩል ሀገራችን በርካታ ፈተናዎችንና የሕልውና አደጋዎችን የተጋፈጠችበት በሌላ በኩል በሕዝባችን፣ በመሪዎቻችን፣ በመከላከያና በፀጥታ ሃይሎች የተቀናጀ ትግል ፈተናዎቹን በፅናት ያለፍንበትና ዓመቱን በድል አድራጊነት የተሽጋገርንበት ወቅት ነው ብለዋል።

ምንም እንኳን በአዲሱ 2015 ዓ.ም መባቻ የኢትዮጵያ ሕዝብ ሰላም አግኝቶ የሀገር ግንባታ ላይ ማተኮር መቻሉ እንደ እግር እሳት የሚያንገበግባቸው የትህነግ ጁንታዎች የመንግስታችንን የተኩስ አቁም ውሳኔ ጥሰው ውጊያ ቢከፈቱብንም የትግራይን ወጣት ለጦርነት ከመማገድ ውጪ በተቀዳጀናቸው ድሎች የተገኙትን ውጤቶች መቀልበስና ቀጣዩን የዕድገት ግስጋሴያችንን መግታት ከቶውንም አይቻላቸውም ሲሉ አስታውቀዋል።

እኛ ወታደሮች ብንሆንም የሰላምን አማራጭ እናስቀድማለን ሰላም ለሀገር ዕድገትና ለሕዝባችን ሕይወት መለወጥ አስፈላጊ መሆኑን ስለምናምን ጦርነት ካልተከፈተብን በስተቀር ወደ ጦርነት አንገባም በማለት ተናግረዋል።

የሀገራችንን ሕልውና አዴጋ ላይ ለመጣልና ሕዝባችንን ለማጎሳቆል ያለመ ሐይል ከየትኛውም አቅጣጫ ውጊያ ከከፈተብን ግን በኡጭር ጊዜና በአነስተኛ ኪሣራ መመከት የሚያስችል ቁመናና ዝግጁነት ላይ እንደምንገኝ ለመላ የኢትዮጵያ ሕዝብ ማረጋገጥ እወዳለሁ በማለት ነው ያስታወቁት።

የሕዝባችንን ሁለገብ ድጋፍና የሠራዊታችንን የዓላማ ጽናት በማቀናጀት በሳል አመራር የሠጡ የሀገራችን መሪዎች የጦር አዛዦች የፀጥታና የደህንነት ኃይሎች የጠላቶቻችን ከበባ በመበጣጠስና አከርካሪያቸውን በመስበር አንፀባራቂ ድሎችን እንድንጎናፀፍ አስችለውናልና ከፍተኛ ምስጋና ይገባቸዋል ብለዋል።

ባለፈው ዓመት በሀገራችን የተለያዩ ክፍሎች ሁከት ሲፈጥሩና ሰላማዊ ዜጎችን የመጨፍጨፍ አረመኔያዊ ተግባር ሲፈፅሙ የቆዩ ፀረ-ሰላም ሀይሎችንም አዳክመን ሀገርን ለማፍረስ አደጋ ወደማይሆንበት ደረጃ ያወረድንበት ዓመት ነው ሲሉም አስታውሰዋል።

ዓለም አቀፍ የሽብር ቡድን የሆነው አልሻባብም የመከላከያ ሠራዊታችንና የፀጥታ ኃይሎቻችን ተጣምረው ባሳረፉበት ጠንካራ ምት ዳግም ኢትዮጵያን በማይተነኩስበት ደረጃ ተቀጥቅጧል፤ ትምህርትም እንዲያገኝ ተደርጓል ያሉት ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ፤ 2014 የፈተና ጊዜና ፈተናዎቹንም በድል ተወጥተን ወደ 2015 የተሸጋገርንበት ዘመን ነው በማለት አስገንዝበዋል።

የጠላቶቻችንን ሀገርን የማተራመስና የማፍረስ ሕልም በተቀናጀ ትግልና ተጋድሎ በመመከታችን ኢትዮጵያ ተስፋ ሰጪ የሆኑ የልማት ውጥኖችን እውን እያደረገች ትገኛለች ሲሉም ተናግረዋል።

በዘመናዊ ትጥቅና በሰው ሀይል አደረጃጀቱ ተልዕኮውን በላቀ ብቃት መወጣት ወደ ሚችልበት ደረጃ የተሸጋገረው ሠራዊት በቀጣይም ዝግጁነቱን እያሳደገ ከየትኛውም አቅጣጫ የሚመጣ ጠላትን እንደሚመክት አረጋግጠዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም