ክልሎች ለመከላከያ ሰራዊት ከ249 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት የሰንጋና የስንቅ ድጋፍ አደረጉ - ኢዜአ አማርኛ
ክልሎች ለመከላከያ ሰራዊት ከ249 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት የሰንጋና የስንቅ ድጋፍ አደረጉ
ጳጉሜን 4/ 2014 (ኢዜአ) የደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች ፣የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች እና የሲዳማ ክልሎች ለመከላከያ ሰራዊት ከ249 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት የሰንጋና የስንቅ ድጋፍ አደረጉ።
የደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች ክልል በዛሬው እለት ከ200 ሚሊዮን ብር በላይ ግምት ያላቸው 1 ሺህ 800 በላይ ሰንጋዎች፣ 2 ሺህ 600 በላይ በግና ፍየል ጨምሮ ከ4 ሺህ ኩንታል ላይ የስንቅ ድጋፍ አድርጓል፡፡
ድጋፉን ያስረከቡት በደቡብ ክልል የድጋፉ አሰባሰቢ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ ስንታዬሁ ወልደሚካኤል፤ የኢትዮጵያ ህዝብና መንግስት ሰላም ፈላጊ መሆኑን ገልጸው፤ ነገር ግን ሰላም በአንድ ወገን ብቻ እንደማይረጋገጥ ተናግረዋል፡፡
በመሆኑም የአሁኑ ትውልድ እንደ ቀደምት አባቶቹ በደምና አጥንቱ የሀገርን ልዑላዊነት እያረጋጠ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ይህን የሀገር አንድነትና ልዑላዊነት ለማረጋገጥ መስዋእትነት እየከፈለ ለሚገኘው የመከላከያ ሰራዊት ሁሌም ደጀን በመሆን እንደሚደግፍም ነው የተናገሩት።
በክልለ በተለያዩ ዞኖች የሚሰሩ የስራ ኃላፊዎች በበኩላቸው አሸባሪው ህወሓት በተደጋጋሚ ሀገር አንድነት እየተፈታተነ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
በተመሳሳይ ዜና የሲዳማ ክልል ከ25 ነጥብ 6 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመቱ 200 ሰንጋዎች፤ 400 በግና ፍየል፣ እንዲሆም ሌሎች የስንቅ ድጋፎችን ያደረገ ሲሆን፤ በተጨማሪ 3 አምቡላንስ ተሽከርካሪዎችን ድጋፍ አድርጓል።
በተጨማሪም የደቡብ ምዕራብ ክልል በበኩሉ 24 ነጥብ 3 ሚሊዮን ብር የሚገመት የእርድ እንስሳና የስንቅ ድጋፍ ነው ያበረከተው፡፡