ቀጥታ፡

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴርና የኢትዮጵያ ሒሳብ አያያዝና ኦዲት ቦርድ የአገልግሎት ክፍያን በቴሌ ብር መክፈል የሚያስችል አሰራር ተግባራዊ አደረጉ

አዲስ አበባ ጳጉሜን 4/2014 (ኢዜአ) የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴርና የኢትዮጵያ ሒሳብ አያያዝና ኦዲት ቦርድ የአገልግሎት ክፍያን በቴሌ ብር መክፈል የሚያስችል አሰራር ተግባራዊ አደረጉ፡፡

ተቋማቱ አገልግሎቱን ያስጀመሩት ከኢትዮ-ቴሌኮምና ኢኖቬሽን ሚኒስቴር ጋር በመተባበር ሲሆን፤  አገልግሎቱን በውጤታማነት ተግባራዊ ለማድረግ በጋራ መስራት የሚያስችላቸውን ስምምነት ተፈራርመዋል፡፡  

ስምምነቱን የኢትዮ-ቴሌኮም ዋና ስራ አስፈፃሚ ፍሬህይወት ታምሩ፣ ኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዶክተር በለጠ ሞላ፣ በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የቆንስላ ጉዳዮች ጀኔራል ዳይሬክተር ሲራጅ ረሽድ እና የኢትዮጵያ ሒሳብ አያያዝ እና ኦዲት ቦርድ ዋና ዳይሬክተር ወይዘሮ ሒክመን አብደላ ተፈራርመዋል፡፡

ስምምነቱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴርና የኢትዮጵያ ሒሳብ አያያዝና ኦዲት ቦርድ የአሰራር ስርዓታቸውን በማዘመን ለደንበኞቻቸው  ቀላልና ፈጣን  አገልግሎት እንዲሰጡ እንደሚያስችል ተመላክቷል፡፡

የኢትዮ-ቴሌኮም ዋና ስራ አስፈፃሚ ፍሬህይወት ታምሩ እንዳሉት፣ ስምምነቱ የተቋማቱን ደንበኞች ጊዜ ጉልበትና እንግልት እንደሚያስቀር ተናግረዋል፡፡

አግልግሎት ሰጭ ተቋማት የደንበኞቻቸውን እንግልት ለመቀነስ አሰራራቸውን በቴክኖሎጅ መደግፍ እንዳለባቸውም ነው ያነሱት፡፡

ኢትዮ-ቴሌኮ የአገልግሎተ ስጪ ተቋማትን አሰራር ዲጂታላይዝ በማድረግ ረገድ የበኩሉን ድጋፍና ትብብር እንደሚያደርግ ነው ያረጋገጡት፡፡

የመንግስት ተቋማት አገልግሎታቸውን በቴክኖሎጂ በመደገፍ ውጤታማ ስራ ማከናወን እንደሚጠበቅባቸው የተናገሩት ደግሞ  የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጅ ሚኒስትሩ ዶክተር በለጠ ሞላ ናቸው፡፡

በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የቆንስላ ጸህፈት ቤት ጀኔራል ዳይሬክተር አቶ ሲራጅ ረሽድ፤ ስምምነቱ የሰነድ ማረጋገጫ ክፍያዎችን በቀላሉ ለመፈጸም ትልቅ አስተዋጽኦ እንደሚያበረክት ገልጸዋል፡፡

ተቋሙ በውጭ አገራት የሚኖሩ ደንበኞች ጭምር እንዳሉት ጠቅሰው፤ ከዚህ አኳያ ስምምነቱ ደንበኞችን ተደራሽ በማድረግ ረገድ ከፍተኛ ሚና አለው ነው ያሉት፡፡

የኢትዮጵያ ሒሳብ አያያዝና ኦዲት ቦርድ ዋና ዳይሬክተር ወይዘሮ ሒክመን አብደላ እንዳሉት የክፍያ ስርዓቱ ዲጂታላይዝ መደረጉ ደንበኞች የምዝገባ እድሳትና ጊዜያዊ የምስክር ወረቀት አገልግሎቶችን በቀላሉ  ለማግኘት ያስችላል፡፡

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር እና የኢትዮጵያ ሒሳብ አያያዝ ኦዲት ቦርድ ዘመናዊ የክፍያ ስርዓቱን ከዛሬ ጀምሮ ተግባራዊ እንደሚያደርጉም ተገልጿል፡፡

አገልግሎቱን ለማግኘት ደንበኞች በቅድሚያ ኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ያለማውን www.eservices.gov.et ላይ በመግባት የሚፈልጉትን አገልግሎት ሰጭ ተቋምና የአገልግሎት አይነት በመምረጥ የአገልግሎት ቅጹን በኦን ላይን መሙላት ይቻላሉ።

ይህን ተከትሎም ለአገልግሎቱ የክፍያ አማራጭ ቴሌብርን በመምረጥ እና ቀጣይ ሒደቶችን በመከተል ክፍያቸውን ያለምንም እንግልት በቀላሉ መፈጸም ይችላሉ፡፡

እስካሁን ባለው ሂደት 25 የመንግስት ተቋማት 326 አገልግሎቶችን በኦንላይን እየሰጡ እንደሚገኝ መረጃዎች ያመላክታሉ፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም