በአዲሱ ዓመት የኢትዮጵያን ሰላም በማስጠበቅ የተጀመሩ የልማት ስራዎች እውን እንዲሆኑ የበኩላችንን ድርሻ እንወጣለን--ወጣቶች - ኢዜአ አማርኛ
በአዲሱ ዓመት የኢትዮጵያን ሰላም በማስጠበቅ የተጀመሩ የልማት ስራዎች እውን እንዲሆኑ የበኩላችንን ድርሻ እንወጣለን--ወጣቶች
ጳጉሜ 4/2014 (ኢዜአ) በአዲሱ ዓመት የኢትዮጵያን ሰላም በማስጠበቅ የተጀመሩ የልማት ስራዎች እውን እንዲሆኑ የበኩላችንን ድርሻ ለመወጣት ዝግጁ መሆናቸውን ኢዜአ ያነጋገራቸው የአዲስ አበባ ከተማ ወጣቶች ተናገሩ።
ሰላምና መረጋጋት የሁሉም ጉዳይ መሰረት መሆኑንም ወጣቶቹ አጽኖት ሰጥተዋል፡፡
ከዚህ አኳያ መንግስት ለሰላም የዘረጋቸውን እጆች ወደ ጎን በመተው የኢትዮጵያን ሰላም ለማደፍረስ ጦርነት የከፈተውን አሸባሪው ህወሓት በመመከት ረገድ ወጣቶች በጋራ መቆም አለብን ነው ያሉት፡፡
ወጣቶች በተለይ የሽብር ቡድኑ ኢትዮጵያን ለማተራመስ የሚጠቀምበትን የሀሰተኛ መረጃ ስርጭት በማጋለጥ የበኩላቸውን አስተዋፆኦ ማበርከት እንደሚጠበቅባቸው ተናግረዋል፡፡
በመሆኑም በአዲሱ ዓመት ሰላም በማስጠበቅ የተጀመሩ የልማት ስራዎች እውን እንዲሆኑ የበኩላችንን ድርሻ እንወጣለን ብለዋል፡፡
ወጣት አቤኔዘር ኤርሚያስ የኢትዮጵያ ጠላቶች በሀሰተኛ መረጃ ህዝቡን ለመከፋፈል የተለያዩ ጥረቶችን እያደረጉ መሆኑን ጠቅሶ፤ ወጣቶች በተቀናጀ መልኩ በኢትዮጵያ ላይ የተከፈተውን የመረጃ ጦርነት ሊመክቱ ይገባል ብሏል።
ወጣት ዮሀንስ ታደሰ እና ወጣት ሙለታ መንግስቱ በበኩላቸው ወጣቶች በየተሰማሩበት የስራ መስክ ለሀገር ሰላምና አንድነት አበክረው ሊሰሩ ይገባል ብለዋል።
ሁሉም በየተሰማራበት ዘርፍ ጠንክሮ በመስራት ለሀገር ሁለንተናዊ ልማት አስተዋፆ ማድረግ እንደሚችል ተናግረዋል።
ወጣቶቹ እንደገለጹት፤ በአዲሱ ዓመት የኢትዮጵያን ሰላምና ደህንነት በማስጠበቅ በኩል ሚናቸውን እንደሚወጡ ነው ያረጋገጡት፡፡
በአዲስ አመት ለኢትዮጵያ ብሩህ ተስፋ እንዲፈነጥቅ ሰላምና አንድነት እንዲሰፍን መልካም ምኞታቸውንም ገልጸዋል፡፡