የአገልጋይነት ቀን የህዝቡን የአገልግሎት እርካታ ለማረጋገጥ ቃል የገባንበት ዕለት ነው - ከንቲባ ሃይሉ ጀልዴ

አዳማ ጳጉሜ 04/2014 (ኢዜአ) ጳጉሜ 4 አገልጋይነት ቀን በአዲሱ ዓመት የመልካም አስተዳደር ችግሮችን ከመሰረቱ ለመፍታትና የህዝቡን የአገልግሎት እርካታ ለማረጋገጥ ቃል የገባንበት ዕለት ነው ሲሉ የአዳማ ከተማ ከንቲባ አቶ ሃይሉ ጀልዴ ገለጹ።

ከንቲባው የዛሬውን የአገልጋይነት ቀን ምክንያት በማድረግ በአዳማ ከተማ ዳቤ ክፍለ ከተማ ጨፌ ቀበሌ በመገኘት ለህብረተሰቡ የአንድ ማዕከል አገልግሎት አሰጣጥ ላይ ተሳትፈዋል።

አቶ ሃይሉ በዚሁ ወቅት እንደገለጹት የዛሬው የአገልጋይነት ቀን በአዲሱ ዓመት የመልካም አስተዳደር ችግሮችን ከመሰረቱ ለመፍታትና የህዝቡን የአገልግሎት እርካታ ለማረጋገጥ ቃል የምንገባበት ዕለት ነው ብለዋል።

"በከተማዋ ከቀበሌ ጀምሮ እስከ አስተዳደሩ ድረስ የተከማቹና የህዝብ ቅሬታ ያለባቸውን ሴክተሮች ለይተን እየሰራንበት ነው" ያሉት ከንቲባው፣ በተለይ የመሬት፣ ገቢዎች፣ ትራንስፖርት፣ ንግድና ማዘጋጃ ቤቶች ላይ አገልግሎቱን ከሰው ንክኪ ነፃ ለማድረግ እየሰሩ መሆኑን ተናግረዋል።

በዚህም የዲጂታል አገልግሎት መስጠት መጀመራቸውን የገለጹት አቶ ሃይሉ፤ ዘመናዊ የመሬት አስተዳደርና አጠቃቀም ካዳስተር፣ የገቢ ግብር አሰባሰብ፣ የንግድ ፍቃድ ክፍያዎችና እድሳት በዲጂታል እንዲሆን እያደረግን ነው ብለዋል።

የዛሬው የአገልጋይነት ቀን አገልግሎታችንን በማዘመን የመልካም አስተዳደር እጦትና ማነቆዎችን በመፍታት የአገልግሎት አሰጣጣችንን ወደ ተሻለ ደረጃ ለማምጣት ዳግም ቃል የምንገባበት ዕለት ነው ብለዋል።

ዕለቱን ምክንያት በማድረግ አስተዳደሩ ደረጃ ያሉ ሁሉም የስራ አስፈፃሚዎችና ሙያተኞች በ18ቱ የከተማዋ ቀበሌዎች ወርደው በዛሬው ቀን የአገልግሎት አሰጣጡን እያገዙ መሆኑን ተናግረዋል።

የአዳማ ከተማ ሲቪል ሰርቪስ ጽሕፈት ቤት ሃላፊ አቶ ኑሜሪ ሸምሱ በበኩላቸው ዕለቱ ሲቪል ሰርቫንቱ በሙሉ አቅሙ የአገልጋይነት መንፈስ ተላብሶ ህዝቡን እንዲያገለግል ንቅናቄ የፈጠረ ቀን ነው ብለዋል።

መንግስት የሚሰጣቸውን አገልግሎቶች በፍጥነት፣ በታማኝነት፣ በቁርጠኝነትና የህዝቡን የአገልግሎት እርካታ በሚያመጣ መልኩ በአዲሱ ዓመት ለማገልገል ቃላቸውን ያደሱበት መሆኑንም ተናግረዋል።

በአገልግሎታችን ላይ ህዝቡ አመኔታ እንዲኖረው በተገልጋዩ ማህበረሰብና በመንግስት መካከል አሁን ያሉትን  ደላሎች ለማስወገድ የሚያስችል የዲጂታል አሰራር ለማድረግ እየሰራን ነው ብለዋል።

የአዳማ ከተማ የመሬት አስተዳደር ሃላፊ አቶ ሳሙኤል ሊዮን እንደገለጹት የመሬት አስተዳደርና አጠቃቀም አገልግሎቱን ለማዘመን የካደስተር ስርዓቱ ተግባራዊ መደረጉን ገልጸዋል።

የዲጂታል አገልግሎቱ በተለይ የመሬት ሀብቱን ከስርቆት፣ ከሌብነትና ዝርፊያ ለመታደግ ወሳኝ መሆኑን የገለጹት ሃላፊው፣ "ህዝቡ ተገቢውን አገልግሎት እንዲያገኝ የተጀመረውን የአገልግሎት አሰጣጣችን ሙሉ በሙሉ ለመለወጥ እየሰራን ነው" ብለዋል።

በመሬት አስተዳደር ጽሕፈት ቤት ሲገለገሉ ያገኘናቸው አቶ አየለ አበበ በበኩላቸው ህዝቡን የሚያዳምጥና ፈጣን ምላሽ የሚሰጥ አመራር እየተፈጠረ መሆኑን ተናግረዋል።

በተለይ የዲጂታል አገልግሎቱ ከተጀመረ ወዲህ ለጉዳይ ወደ መሬት አስተዳደር ስመጣ ፈጣን ምላሽ እየተሰጠ መሆኑንና አሁንም ይበልጥ አገልግሎቱን ማዘመን እንደሚያስፈልግ አመልክተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም