በአዲሱ ዓመት የክልሉን ሰላም በማጠናከር የህዝቡን ተጠቃሚነት በሚያረጋግጥ ልማት ላይ በትኩረት ይሰራል- የጋምቤላ ክልል ርዕሰ መስተዳድር - ኢዜአ አማርኛ
በአዲሱ ዓመት የክልሉን ሰላም በማጠናከር የህዝቡን ተጠቃሚነት በሚያረጋግጥ ልማት ላይ በትኩረት ይሰራል- የጋምቤላ ክልል ርዕሰ መስተዳድር
ጋምቤላ፤ ጳጉሜን 4/2014 (ኢዜአ) በአዲሱ ዓመት የክልሉን ሰላም ይበልጥ በማጠናከር የህዝቡን የልማት ተጠቃሚነት በሚያረጋገጡ የልማት ዘርፎች ላይ በትኩረት እንደሚሰራ የጋምቤላ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኡሞድ ኡጁሉ አስታወቁ።
ርዕሰ መስተዳደሩ አዲሱን ዓመት አስመልክተው ለጋዜጠኞች እንደገለጹት፤ በ2014 የስራ ዘመን እንደ ክልልም ሆነ እንደ ሀገር በውስጥና በውጭ ጠላቶች የተደቀኑ ፈተናዎችን በአሸናፊነት በመሻገር በርካታ ድሎች የተመዘገቡት ነው።
በቀጣዩ አዲስ ዓመትም በክልሉ ያለውን ሰላም በማጠናከር ህዝቡን ተጠቃሚ በሚያደረጉ የግብርና፣ የትምህርት፣ የጤናና ሌሎች የልማት ስራዎች ላይ በትኩረት እንደሚሰራ አስታውቀዋል።
በፍትህና በሌሎች ተቋማት ያለውን አገልግሎት አሰጣጥ በማሻሻል በህዝቡ የሚነሱ የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች ምላሽ የመስጠቱ ተግባር ሌላው የክልሉ መንግስት የትኩረት አቅጣጫ መሆኑን ገልጸዋል።
በክልሉ በዘንድሮው ክረምት በወንዞች ከአቅም በላይ መሙላት ምክንያት ባስከተሉት ጎርፍ 187 ሺህ ህዝብ መፈናቀሉን ጠቅሰው፤ በአዲሱ ዓመት እነዚህን ወገኖች በዘላቂነት የማቋቋም ስራ እንደሚከናወን ተናግረዋል።
የህወሓት የሽብር ቡድን ከተላኪዎቹ ሸኔና ጋነግ ጋር በመሆን በክልሉ ለመፈፀም የተሞከረው እኩይ ተግባር በመመከት የተገኘውን ሰላም አስጠብቆ ለማስቀጠል የክልሉ መንግስት ህዝባዊ ደጀንነት በማጠናከር በትኩረት እንደሚሰራ አስታቀዋል።
አዲሱ ዓመት ለመላው የክልሉና የኢትዮጵያ ህዝቦች የሰላም፣ የፍቅርና የብልጽግና ዘመን እንዲሆንል ርዕሰ መስተዳድሩ መልካም ምኞታቸውን አስተላልፈዋል።